Wednesday, October 5, 2011

መልካም አስተሳሰብ

ስለቀና አስተሳሰብ ብዙ ተብሏል። ምን እንደሆነ ከማስረዳት ጀምሮ ሊያመጣው የሚችለውን ነገር በመተንተን የሃይማኖት ሰዎችም ሆኑ የስነ  ልቦና  ጠበብቶች ብዙ ይናገራሉ ይጽፋሉ። ጉዳዩን ለማሳወቅም ሆነ  ለማወቅ ጊዜ  የሚጠፋበት ምክንያት ከፍተኛ  ጠቀሜታ ስላለው ነው። ጠቃሚነቱም የሚመነጨው ሀሳብ ጉልበት (Energy) ነው ከሚለው ነው። ጉልበት ነው ስንል በአንድ በኩል አዎንታዊ ጉልበት ሊሆን ሲችል በሌላ  በኩል ደግሞ ኢ_አዎንታዊ (Negative) ሊሆን ይችላል።


ቀና  አስተሳሰቦች አዎንታዊ ጉልበት ያመነጫሉ ኢ_አዎንታዊ አስተሳሰቦች ደገሞ ተቃራኒውን በጎ ያልሆነውን ባለቤቱንና አካባቢውን የሚጎዳውን ጉልበት ያመነጫሉ።  ታዲያ  የዚህን  ምስጢር የተረዱ ምርጫቸው  ቀና  አስተሳሰብ እንዲሆን ይጥራሉ። በአገራችንም "ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ" የሚል አባባል አለ። ቀና አስተሳሰብ በመጀመሪያ የሚጠቅመው ባለቤቱን ነው። ቀና ያልሆነ አስተሳሰብም ደግሞ በመጀመሪያ  የሚጎዳው ሃሳብ አሳቢውን ባለቤቱን ነው። ይህም በኒውተን የድርጊት ሕግ (Newton's Law of Action - for each action there is an equal and opposite reaction) ከሚለው ጋር የሚሄድ ይሆናል። ስለዚህ ቀና  ሃሳብ ያሰበ  የቀናውን ውጤት ያገኛል።  በተቃራኒው ያሰበ  ደግሞ ለአስተሳሰቡ ተገቢ የሆነውን ቀና ያልሆነውን ውጤት ያገኛል። አንድን ነገር ለመሥራት የተነሳሳ ሰው ቀና  ውጤት ለማግኘት አንደሚችል ከወዲሁ ማሰብ ይኖርበታል። ቀና ያልሆነ ነገር እያሰብ የሚሳካለት ሰው ብዙ አይኖርም። 
ስፖርተኞች አሸናፊነታቸውን  ከማረጋገጣቸው በፊት  በአእምሮአቸው አሸንፈው ማየት ይኖርባቸዋል።  ያ  ቀና  አስተሳሰብ ነው ለድል 
የሚያበቃውን  ጉልበት የሚያመነጨው።መውደቁን የሚያስብ ተማሪ ውጤቱ መውደቅ  ይሆናል። ስለዚህ በማንኛውም ጉዳይ ዙሪያ በይሆናል ቀና  አስተሳሰብ መሄድ ለጤናም መልካም ከመሆኑ ባሻገር ለሁኔታው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ማሸነፉን እየተጠራጠረ  ውድድር ውስጥ የሚገባ  ስፖርተኛ  ያሸንፋል ብዬ አላስብም።   አሸናፊ የሚሆኑት ሁሉ በማሸነፋቸው ቆርጠው የገቡ ናቸው።

... ይቀጥላል

Tuesday, October 4, 2011

ፍቅር ምንነቱና አስፈላጊነቱ

ነጋ ዓለማየሁ 
ሲልቨር ስፕሪንግ፣ ሜሪላንድ

1.    ፍቅር
ፍቅር ትልቁና ዋነኛ ነገር እንደሆነ እየሱስ ክርስቶስ እራሱ አስተምሯል። ፍቅር አንድን ሰው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል ነው እግዚአብሔር እንዲሁ አለምን ወዷልና። "በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይዎት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና።" (ዮሐ 3፡16) ስለተደረገልን ነገር ብለን ሳይሆን እንዲሁ ስንወድ ፍቅር ይባላል። ፍቅር ተቀብሎ በመስጠት ሂሳብ የተመሰረት አይደለም። በዚህም ምክንያት ፍቅር ትልቅ ግንኙነትን የማዳን ኃይል አለው። ፍቅር ከጥላቻ የበለጠ አቅም አለው። ማፍቀር በእግዚአብሔር ለሚያምኑ የግድ ነው። ይህንንም አስመልክቶ ቅዱስ መጽሐፍ “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።” (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4:8) ይለናል። ስለዚህ ሰዎች ለእኛ ጥሩ በሚሆኑበት ጊዜ ወይም በተሳካላቸው ጊዜ የምንሰጠው ፍቅር ሳይሆን ከዚህም ውጭ ሲሆኑ የምንሰጣቸው ነገር ነው በፍቅር ስጥ ሊካተት የሚችለው። ፍቅር ሰጪ እጁን እንጂ ተቀባዩን አያሳይም።
ለክርስቲያኖች ይህንን መረዳት ቀላል ሊሆን ይገባል። ክንያቱም እግዚአብሔር አንድ ልጁን ለፍቅር መስዋዕት አቅርቧልና። እየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ያደረገው መልካም ነገር ፍቅር አስይዞት አይደለም ራሱን አሳልፎ የሰጠው እንዲሁ ሰውን በማፍቀሩ እንጂ። እኛም የቤተሰብ አባል የሆኑትንም ሆነ ሌሎችን እንዲሁ እንድንወዳቸው ከዚያም የፍቅርን ምላሽ ልናገኝ እንችላለን። ፍቅር አለን የምንልም ሁሉ ከዚህ አንጻር እራሳችን መጠየቅ አለብን። የምናፈቅራቸው ሰዎች አንድ ወይም ሁለት ነገራቸው ቢለወጥ ምን እንላለን? የምንከባከባቸው ሰዎች ባላሰብነው መንገድ ቢሄዱ ምን ይሰማናል? ያለቅድመ ሁኔታ ማፍቀር የሚለው በትክክል ከተረዳነው እነዚህን ሰዎች ስናፈቅራቸው ተበላሸ የምንለው ነገር እንዲድን እግዚአብሔር ይረዳል።
ለሰው መቸም መልካም የሚያደርግለትን መውደድ ቀላል ነገር ነው። የሚጠላውን መውደድ ግን በጣም ከባድ ነገር ነው። ደንጋይ የሚወረውርብህን ውደድ ማለት ሞኝነት ይመስላል። እንዲያውም ሁለተኛ ደንጋይ እንዳይወረውር ቋጥኝ የሚያክል ደንጋይ አንስቶ መውገር የሚሻል ይመስለናል። እግዚአብሔር ግን ሰውን ወደደ ከመውደዱም የተነሳ አንድ ልጁን ለሰው ልጅ የኃጢአት ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ለመስዋዕት እንዳቀረበ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ስጦታ የሚሰጠው ለሚወዱት ነው። እግዚአብሔር ታዲያ በእውን ወዶናልና ታላቁን ስጦታ ሰጠን። ሆኖም ግን የሰው ተግባር ለስጦታ የሚያበቃ ነበር ወይ? ሰው በኃጢአት ደክሞ ይህ ነው የማይባል ርኩሰትን እየፈጸመ ባለበት ጊዜ እግዚአብሔር ግን ታላቁን ነገር አደረገለት።
እግዚአብሔር የሰውን በደል፣ ደካማነትና የመንፈስ ጉስቁልና ሳይመለከት እንዲሁ ወደደው። "አንተ ጥሩ ነህ መልካም ሥራ ሠርተሀል" ብሎ ሳይሆን "አንተ የእኔ ነህ ምንም አድርግ ምንም የእኔ ነህና አልተውህም" በማለት በፍቅሩ ጎበኘው። ትክክለኛው ፍቅር ምንም ቅድመ ሁኔታ የለውምና። ለፍቅር ቅድመ ሁኔታ ከተበጀለት ፍቅር ሳይሆን የንግድ ሥራ ወይም ተቀብሎ ተመጣጣኝ ዋጋ መክፈል ነው። ቅድመ ሁኔታ አበጅተን የሚወዱንን ወይም መልካም ያደረጉልንን ለመውደድ መለኮታዊ ኃይል ወይም መንፈሳዊነት አያስፈልገንም። መንፈሳዊነት የሚያስፈልገው የሚጠሉንንና የሚረግሙንን ለመውደድ ነው።
የደካሞችን ችግር ማየት እንደለለብንና እንዲያዉም ሸክማቸውን ልንሸከም እንደሚገባ የክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።”(ገላትያ 6፡2) ታዲያ ስህተት ብናይም ስህተቱን ለመጋራት መፈለጋችንና የራሳችን እንደሆነ መገንዘቡ ፍቅራችን ያለቅድመ ሁኔታ እንዲሆን ይረዳናል።

1.1 መግቢያ

ፍቅር ከንፈ ፍሬዎች አንዱ መሆኑን የክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ ወደ ገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ "የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።" (ገላትያ 5፡22) እያለ ያስተምረናል። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሁሉም የምትበልጠዋ ትእዛዝ ፍቅር መሆኗን "ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፥ ባልንጀራህን እንደነፍስህ ውደድ የምትለው ናት" (ማቴ 22፡ 37-39) ብሎ ዘላለማዊ በሆነው ቃሉ ያስተምናል። ፍቅርም ለሚያፈቅሩን ወይም በጎ ላደረጉልን ብቻ ሳይሆን የሚጠሉንም ሆነ የሚረግሙንን እንድንወድ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ያዘናል "እኔ ግን እላችኋለሁ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሟችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።" (ማቴ 5፡ 44-45) በመሆኑም ፍቅር ታላቅና አቢይ ነገር ነው ማለት ነው። ዚህ በፍቅር ዙሪያ እግዚአብሔር እንደፈቀደ የሚከተለውን ትንታኔ አቅርቤአለሁ።

1.2 ፍቅር ምንድን ነው?

ፍቅር ዋናና መለወጫ የሌለው ነገር ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። ስለዚህ ዋናው ነገር የፍቅርን ምንነት መረዳቱና መተግበሩ ነው እንጂ አስፈላጊነቱን ማወቁ አይደለም። ለሰው መቸም መልካም የሚያደርግለትን መውደድ ቀላል ነገር ነው። የሚጠላውን መውደድ ግን በጣም ከባድ ነገር ነው። ደንጋይ የሚወረውርብህን ውደድ ማለት ሞኝነት ይመስላል። እንዲያውም ሁለተኛ ደንጋይ እንዳይወረውር ቋጥኝ የሚያክል ደንጋይ አንስቶ መውገር የሚሻል ይመስለናል። እግዚአብሔር ግን ሰውን ወደደ ከመውደዱም የተነሳ አንድ ልጁን ለሰው ልጅ የኃጢአት ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ለመስዋዕት እንዳቀረበ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ስጦታ የሚሰጠው ለሚወዱት ነው። እግዚአብሔር ታዲያ በእውን ወዶናልና ታላቁን ስጦታ ሰጠን። ሆኖም ግን የሰው ተግባር ለስጦታ የሚያበቃ ነበር ወይ? ሰው በኃጢአት ደክሞ ይህ ነው የማይባል ርኩሰትን እየፈጸመ ባለበት ጊዜ እግዚአብሔር ግን ታላቁን ነገር አደረገለት።
          እግዚአብሔር የሰውን በደል፣ ደካማነትና የመንፈስ ጉስቁልና ሳይመለከት እንዲሁ ወደደው። "አንተ ጥሩ ነህ መልካም ሥራ ርተሀል" ብሎ ሳይሆን "አንተ የእኔ ነህ ምንም አድርግ ምንም የእኔ ነህና አልተውህም" በማለት በፍቅሩ ጎበኘው። ትክክለኛው ፍቅር ምንም ቅድመ ሁኔታ የለውምና። ለፍቅር ቅድመ ሁኔታ ከተበጀለት ፍቅር ሳይሆን ሌላ ቢባል ይሻላል። ቅድመ ሁኔታ አበጅተን የሚወዱንን ወይም መልካም ያደረን ለመውደድ መለኮታዊ ኃይል ወይም መንፈሳዊነት አያስፈልገንም። መንፈሳዊነት የሚያስፈልገው የሚጠሉንንና የሚረግሙንን ለመውደድ ነው።
የክርስትና ሃይማኖት ዋና ፍሬ ነገር (Essence) ፍቅር ይመስለኛል። የሰው ልጅ በአዳም ምክንያት ከገነት ተባሮ በጢአት ዓለም ይኖር ነበር። ምንም እንኳ አዳም በገዛ ሥራው ከገነየወጣ ቢሆንም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከመውደዱ የተነሳ ሊያድነውና ከመጥፎ ሥራው አውጥቶ ወደ ቀደመ ማዕረጉ እንዲመለስና የዘለዓለም የደስታ ሕይዎት ሊሰጠው ፈለገ። ፍቅር ድክመትን አያይምና እግዚአብር አምላክ የሰውን ልጅ ድካምና ጢአት ሳይመለከት ሊያድነው በመውደዱ አንድ ልጁን ወደዚህ ዓለም ላከ። "በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይዎት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና።" (ማቴ 3፡16)
የእግዚአብሔር አብ የባህሪ እኩያ የሆነው እግዚአብሔር ወልድም የእኛን መከራ ተቀብሎ እናንተ አትችሉም እኔ ዕዳችሁን ልክፈልላችሁ ብሎ በጢአተኞች እጅ ተገርፎና በምስማር ተቸንክሮ የጢአታችን ዕዳ ከፈለ። ይህ ለምን ሆነ ቢባል ለፍቅር የተከፈለ ዋጋ ነው ይባላል። በዓለማችንም የሚዋደዱ ቤተዘመዶች ውስጥ አንዱ የተበደረውን የገንዘብ ዕዳ ሌላኛው እንደሚከፍል ሁሉ ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ከዚያም ቀጥሎ የተቆረሰውን ሥጋዬን ብትበሉ የፈሰሰውን ደሜን ብትጠጡ መለኮት ለዘላለም እንደሚኖር ሁሉ እናንተም የዘላለም ሕይዎት ታገኛላችሁ ብሎ አወጀ። ከፍቅሩ ብዛት ሰውም እንደእሱ ለዘላለም ሕይዎት እንዲኖረው አደረገ።
ይህ እንግዲህ አምላክ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ያመለከተ ታላቁና አቢይ ተግባር ሲሆን የፍቅርን ምንነት የገለጸና ያስተማረ ነው። እግዚአብሔር በኦሪት ለሙሴ የሰጠው ሕግጋትም ቢሆን ዋናው ቁም ነገር ፍቅር ነው። እነርሱም ሰው ለእግዚአብሔር፤ ሰው ለባልንጀራው ሊኖረው ስለሚገባ ፍቅር ተብሎ ሊጠቃለል ይችላል። ለዚህም ነው ክርስቶስ ከለይ እንደተጠቀሰው የፊተኛይቱና ሁለተኛይቱ ብሎ የሚገልጻት። አምላክ የሰውን ልጅ እወድሀለሁ ሲለው "ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ" አለው። ለአንተ ያለኝ ፍቅር የጠና ነውና አንተም እኔን ልትወደኝ ይገባል። በመካከላችን ሌላ ልታስገባ አይገባህም ወይም ደግሞ እኔን ልትተካኝ አትችልም ማለቱ ይመስለኛል።
ከዚያም ሰው ለባልንጀራው ሊኖረው የሚገባውን ፍቅር ሲገልጽለት አትግደል፣ አታመንዝር፤ በሐሰት አትመስክር፤ ንብረቱን አትመኝ እያለ አዘዘው። ሰው የሚወደውን አይገድልምና፣ ከሚወደው ላይ አያመነዝርምና፣ በሚወደው ላይ በሐሰት አይመሰክርምና፣ የሚወደውንም ሰው ንብረት አይመኝምና በአጭሩ አፍቅረው ወይም ውደደው አለው። ሰው እግዚአብርንና ባልንጀራውን ከወደደ ምን ችግር ሊኖርበት ይችላል?
ሰዎች በዘመናችን በትንሹም በትልቁም ጉዳይ ቂም ተያይዘው ይቅር ማለት ይቸግራቸዋል። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት ትክክለኛው ፍቅር ባለመኖሩ ነው። ፍቅር ሁልጊዜ ይቅር ባይ ነው። ለነገሩ ሰው ፍቅር ካለው ቅሬታ የሚባለው ነገር ከመጀመሪያውም አይመጣም። ክርስቶስ ፍቅሩን አይቶ ጢአታችን ሳይመለከት እኛን ለማዳን ከሰማይ እንደወረደ ሁሉ ፍቅር ያለው ሰው የሌላውን ስህተት አያይም። ከዚህ አንጻር ፍቅር እውር ነው ሊባል ይችላል። እውርነቱም ደግ ያልሆነውን ነገር ባማየቱ ነው። በፍቅር የደረጀው ስብዕና ሌላ መጥፎ ነገር ሊያሳየው አይችልም።
በሌላ በኩል ደግሞ ፍቅር አካላዊ ይን ሊያየው የማይችለውን ረቀቅ ያለውን የሰው ልጅ ንጹህ ባህሪ ሊያይ የሚችል አጉሊ መነጽር ነው። በሁለቱ አካላዊ አይኖቻችን ልናየው የማንችለውን ውበትም ሆነ መልካም ባህሪ በፍቅር ግን ልናየው እንችላለን። አባቶቻችን ሲተርቱ "የወለደና የጋገረ ጅል አይልም" ይላሉ። ይህም የሆነበት ምክያት ወላጆች ለልጆቻቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ ነው። ፍቅር ሲኖር ሁሉ ነገር ይኖራል። ፍቅር ትእግሥተኛ፣ ይቅር ባይ፣ ተባባሪ፣ አክባሪ፣ አስተዋይ፣ አዋቂ፣ አንድነት፣ እውነት በመሆኑ ሌላውን በሚገባ ለማየት ያስችላል። ሁሉም ነገር ኑሮት በፍቅር ማጣት የተነሳ እነዚሁ የጎደሉት ሰው አረም የሞላበት ጓሮ እንደማለት ነው። አረም የሞላበት ጓሮ ደስ አይልም። አላፊ ግዳሚውም "ይኸ የሰነፍ ሰው ጓሮ" እያለ ያልፋል። ምንም ንብረት ሳይኖረው ፍቅር ቢኖረው ግን ንጹህ ጓሮ አለውና ያየው ሁሉ ሊከራየው፣ ሊገዛው፣ ጊዜውን ሊያሳልፍበት ይፈልጋል። ከዚያ ጋር ተያይዞም በሚመጣው ሲሳይ ከፍ ያለ ሀብትና ደስታ ያገኛል ማለት ነው።
ስለዚህ በቅርብ የምናውቃቸውንም ሆነ  የእግዚአብሔር ፍጡር የሆነውን ማንኛውንም ሰው   ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ልናፈቅ ይገባል። በኑሮአቸው መልካም ነገር ስለገጠማቸው ወይም ጥሩ ያልሆነ ነገር ስለገጠማቸው የእኛን ፍቅር ሊለውጠው አይገባም። ለምሳሌ ልጀ በትምህርቱ ጥሩ ጤት አላመጣም፤ ባለቤቴ መልካም ነገር አላደረገልኝም/አላደረገችልኝም፤ እከሌ ሰላምታ ከለከለኝ እና የመሳሰሉትን እያልን ፍቅር ከቀነስን ቅድመ ሁኔታ አዘጋጀን ማለት ነው። በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተው ፍቅር ደግሞ ፈተና ይበዛበታል። ከዕለታት አንድ ቀን የተቀመጠው መሥፈርት ቢጓደል ፍቅር ችግር ላይ ይወድቃል። እንደዚሁ ያለውን "ፍቅር" ታዲያ ፍቅር ሳይሆን የህብረት ስምምነት ወይም በውለታ ላይ የተመሠረተ "ፍቅር" ወይም ግኑኝነት ሊባል ይችላል። 

1.3 ፍቅር ለምን ያስፈልጋል?

እግዚአብሔር ሰውን እንዲሁ የበላይነቱን ለማሳየት ሲል ያዘዘው አንዳችም ነገር ያለ አይመስለኝም። ሐኪም አንድ በሽተኛ ከበሽታው እንዲድን መድሐኒት እንደሚያዝለት ሁሉ የሐኪሞች ሐኪም የሆነው ዘመን የማይሽረው እግዚአብሔር አምላክም የሰው ልጅ ጤነኛና ደስተኛ ሆኖ ይኖር ዘንድ ትእዛዛትን ሰጥቶታል። ትእዛዛቶቹም በደስታ፣ በጤንነት፣ በሰላም እንዲኖር የተሰጡት መድሃኒቶች (Prescriptions) ናቸው። አፍቅር የሚለውም ከዚያ የመነጨ ነው።
ሰው በጣም የሚጠላውንና በጣም የሚወደውን ሰው እኩል ነው የሚያስታውሰው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው በሰው ቅር በተሰኘ ጊዜ በጣም በተቀየመ ጊዜ ያንን ያስቀየመውን ሰው አሁንም አሁንም ያስታውሰዋል። ቅር ያሰኘውን ሰው መርሳት ቀላል ነገር አይደለም። እንዲያውም እንደነገሩ አሳሳቢነት ጉዳዩን ያወቁ ቤተሰቦች ወይም ጓደኞች ሁኔታውን ለማረሳሳት ቢሞክሩም በቀላሉ የሚተው አይደለም። በተመሳሳይ ሁኔታም የሚወደውን ሰው አሁንም አሁንም ያስታወሳል። በሁለቱ መካከል በማስታዎስ ረገድ ልዩነት አይኖርም። ሆኖም ግን ሐሳቦቹ ያላቸው ተጽእኖ ልዩነት የሲኦልና የገነት ያህል ነው።
          ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው የጠላውን ሰው ባስታወሰ ጊዜ ተጠይው የተናገረው መጥፎ ቃል ወይም ያደረገው መጥፎ ድርጊት ይታወሰውና እያንዳንዷ ትእይንት ኢአወንታዊ (Negative) ኃይል ሆና ሰውየውን ቀስ በቀስ መንፈሱን ታደክመዋለች፥ የአካሉ ሕዋሳቶችም የሥራቸውን ሂደት ለወጥ ያደርጋሉ። ይኸ ሰው በዚያ ሰዓት ፊቱን በመስታዎት ቢመለከት ጥሩ ያልሆነ ሃሳብ ምን አይነት ተጽእኖ እንዳለው መረዳት ይችላል። ጨጓራውም አሲድ ይረጭና ማቃጠል ይጀምራል። መላው የሰውነት ህዋሳትም በጣም ስሜታዊ (sensitive) በመሆኑ የደም ግፊቱም ይጨምራል። ይህ ከብዙ በጥቂቱ የሚያደርሰው ችግር ነው። የሚገርመው ነገር ተጠይው ሰው ይህን ያህል ጉዳት ማድረሱን አለማወቁ ነው።
          በተቃራኒው ደስ የሚለንን ነገር ወይም የምንወደውን ሰው ባስታወስን ጊዜ የሰውነታችን ህዋሳቶች ሁሉ ይፍታታሉ። ፊታችን ሁሉ በፈገግታ ይሞላል። በዚያ ወቅትም የሙሉ ጤነኛ ስሜት ይሰማናል። እራሳችን በመስታዎት ብናይም በቅሬታ ጊዜ ከምናየው ጋር ያለውን ልዩነት እናያለን። ታዲያ ማን አለ ልጁ በሥጋው እንዲሰቃይ ወይም ችግር እንዲደርስበት የሚፈልግ? ወላጆች ልጆቻቸውን ምንም ወንጀል እንዳይሠሩ ይመክራሉ። ይኸንም የሚያደርጉበት ምክንያት ልጆቹ ወንጀል ከሠሩ የሚደርስባቸውን ቅጣት ስለሚያውቁ ነው። በተመስሳይ ሁኔታ ጊዜ የማይወስነው፤ ያለፈውን፣ የአሁኑን የወድፊቱንም የሚያውቀው እግዚአብሔር አምላካችን አባታችን ለልጆቹ ሰላም ሊሰጣቸው፤ ደስተኛና ጤነኛ ሊያደርጋቸው የሚችለውን ነገር ትእዛዝ ብሎ ሰጥቶናል። ለዚህም ነው 'አፍቅር' ብሎ ያዘዘን።
ሐኪም የታዘዘልህን መድሐኒት ካልወሰድክ በሕይወትህ ላይ ችግር ታመጣለህ እንደሚለው ሁሉ፥ እግዚአብሔርም ካላፈቀርክ በምድርም በሥጋህ ስቃይን ታበዛለህ። በኋላም ለነፍስህ ዘላለማዊ ሕይዎት የሚገጥምህ አሁን የዘራኸው የዘርህ ፍሬ አዝመራ ነውና መልካም ነገር አይገጥምህም። ጎበዝ ገበሬ መልካም አዝመራ ከማዝመሩም በተጨማሪ ከወዲሁ ደስተኛ እንደሚሆን ሁሉ እኛም የፍቅርን ህግ ካከበርን በምድርም ደስተኞች እንሆናለን።

1.4 የሚጠሉንን እንዴት ልንወድ እንችላለን?
"መቀየሜን ትቸ ማፍቀር እንዳለብኝ እኮ ይገባኛል። ኖም ግን እንዴት ይቻላል? ይህ የሚጠሉንን ማፍቀር የሚባለው ነገር ለማለት ካልሆነ በስተቀር ለመፈጸም ከባድ ነው።" እነዚህና የመሳሰሉ አባባሎች የተለመዱ ናቸው። አንዳንድ መምህራን ሳይቀሩ "በእሱ ቸርነት እንጂ በሥራችን አንድንም" ው ይደመድማሉ። ይኸ አባባል እውነታነት አለው። የሚጠሉንን ማፍቀር ቀላል ነገር አይደለም። ለዘመናት አብሮ የቆየን ነገር ማስወገድ ከባድ ነገር ነው። አንድ ባልሆነ ሱስ የተለከፈ ሰው እንኳ ያንን ሱሱን ለመተው በጣም ይቸገራል። ሆኖም ግን ለመተው የቆረጠ እንደሆነ የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅሞ ሊያቆም ይችላል። ይህም ሰው መረዳት ያለበት ነገር በአንድ ሌሊት የሚሆን ነገር አለመኖሩን ነው። ክርስቶስ የሚጠሉንን እንድንወድ እንዲህ ሲል ያስተምረናል "ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፥ የሚረግሟችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድልዋችሁም ጸልዩ" (ሉቃስ 6፡27-28) እግዚአብሔር የማይሆንን ነገር አይናገርም አያዝምና ይህ ቃል ትክክል ነው ማለት ነው። ይ ከሆነ "አይቻልም" የሚለውን የራስን ራዕይና ይኸንኑም የማሳካት ተግባር (Self fulfilling prophecy) ትተን በ"ይቻላል" መቀየር አለብን። ክርስቶስም ተዋደዱ ብሎ ሲያዘን በእሱ ማድረግ የማንችለው ነገር እንደለለ ያበስርልናል።
          ጥላቻን ለማስቀረት ከሚጠቅመው ነገር ዋነኛው ነገር እራስን ማወቅ ነው። የእራስን አካላዊ ወይም ሥጋዊ ማንነት ሳይሆን መንፈሳዊ ማንነትን መረዳት አስፈላጊ ነው። እራስን በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በእድሜ፣ በትምህርት ደረጃ፣ በሙያና በመሳሰሉት ለይቶ ማወቅ ከሥጋ ጋር የተያያዘ እውቅና ነው። ይህ እውቅና ሥጋ ውስን እንደሆነ ሁሉ ውስን ነው። ሥጋና ነፍስም ኮንትራታቸውን ሲጨርሱ የሚቀር ነው። ዋናውና ነጻ የሚያወጣው እውቀት ወይም እውቅና ከእግዚአብሔር የሚገኘው የመንፈስ ወይም የነፍስ እውቅና ነው። ማነታችን በሚገባ ስንረዳ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዮስ ሰዎች በላከው ደብዳቤ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊል 4:13) የሚለው እውን ይሆናል። መንፈሳዊ ማንነትን ሳይረዱ የመንፈስን ባህሪዎች መላበስ አስቸጋሪ ነው።
          ይህንን ጽንሰ ሐሳብ በሚከተለው ምሳሌ መግለጽ እፈልጋለሁ። ወደ አገረ አሜሪካ መግባት የፈለገ ሰው የአሜሪካን ፓስፖርት ወይም የአሜሪካ ቪዛ ያስፈልገዋል። ከእነዚህ አንዱን ካልያዘ የመግቢያ ፈቃድ አይሰጠውም። በተመሳሳይ ሁኔታም ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ነውና በሥጋ ባህሪ ልንረዳው ወይም ልንፈጽመው አንችልም። በሥጋ እውቀት የመንፈስን ባህሪ ለመተግበር መሞከር ማለት ወደ አሜሪካ ለመግባት ቪዛ የሌለው የኢትዮጵያን ፓስፖርት እንደማሳየት ማለት ነው። ማንነታችን ስንረዳ ከየትኛው ወገን እንደሆንን ማወቅ ያስችለናል። "እኔ ከማን/የማን ነኝ?" ብሎ ራስን መጠየቅ አስፈላጊ ነው። የእግዚአብሔር መሆናችንን ስንረዳና በእውነት እግዚአብሔር የሚፈቅደውን ስናደርግ የእርሱን ኃይል መጠቀም እንችላለን ለዚህም በመጀመሪያ ጽድቁን እንድንሻ "ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።" (ማቴ 6፡33) እያለ ክርስቶስ በሕያው ቃሉ የሚያስተምረን።