Thursday, February 7, 2013

ሲያቀብጠኝ ነው ወይስ ሲፈትነኝ?


ሲያቀብጠኝ ነው ወይስ ሲፈትነኝ

ሲያቀብጠኝ ነው ወይስ ሲፈትነኝ፣
እዚያ ወስዶ የከተተኝ።
እያልኩ እራሴን ብጠይቅ፣
መልስ ለማግኜት ብጨነቅ።
ፈተና ነው እለፈው፣
ሲያስፈልግም ተወው።
ይለኛል የእራሴ ድምጽ፣
ሳያሰማ ምንም አመጽ።
መጀመሪያ ሲመርጡኝ፣
ለምነው ነበር ያስገቡኝ።
እምቢ ብትል ብትሸሽ እንደ ዮናስ፣
ጥሪህን አልቀበል ብለህ የኃያሉን ንጉሥ፣
መሄጃም የለህ ማምለጫ የትም አትደርስ።
ብለው ወንድሞች ሲነግሩኝና ሲማጸኑኝ፣
እኔም እሺ ብየ እያቅማማሁ ገባሁኝ።  
እኔም አንድ ሐጢያተኛ።
ያለስህተት የማልተኛ።
አምላኬን የምበድል በጧት በማታ።
ምስጋና ቅዳሴ የማጎድል እንዲሁም እልልታ።
ይህንንስ አውቃለሁ፣
ነጋሪም አልፈልግም ሁልጊዜ አለቅሳለሁ።
አስታዋሺም አልሻ፣
አምላኬም ያውቃል እንዳለብኝ የመንፈስ ልምሻ።
ስለእኔ ችግር መናገር ምን ሊጠቅም፣
ከእዳ ነጻ አያወጣ ከድካም አያገግም።
አምላክ እንደሆን ከእነ ድክመቴ ያውቀኛል፣
ተገርፎም በመስቀል ላይ ሞቶልኛል፣
ከሞትም አድኖኛል።
ነጋ ሲሉ አልነጋም አኩኩሉ ጨዋታ።
እንጫወት ለአፍታ፣
ይላል ሥራ ሊያስፈታ።
ሰዓቱ የማን ሆኖ የምንጫዎትበት፣
አይጠቅምም ብናቀርበው ለአምላካችን መስዋዕት።
እያንዳንዷ ጊዜ ከሳሹ ያጠፋት፣
ለመልካም ሳይሆን ለክፋት፤
ባለቤቱን ያሳዝናል፣
ለኪሳራም ይዳርጋል።
መስሏቸው ነበር የምንተወው ክሱ አሰልችቶን፣
አምላክ ግን በጥበቡ ለእኛ ጉልበትን ሰጥቶን፤
ይኸውና እንሰራለን ለበረከት እንደክማለን፤
እኔ ግን እላለሁ ለከሳሹም እንጸልይ፣
አብረን ነውና ያለነው በምድር አይደለም በሰማይ።
እሳት ቢነሳ በጎረቤት፣
ይደርሳልና ከቤት።
አብሮ ማጥፋት ነው ተባብሮ፣
ያለውን መሰናክል ሰብሮ።
ካልሆነ ያወድመናል፣
ሁላችንም ይበላናል፤
ታዲያ ጎበዝ አይዞን እንበል
ሞት እንደሆን አይቀርም
ስም ግን አይቀበርም፤
መልካም ሠርቶ  ማለፍን፣
ለመጪው ትውልድ መተካትን፣
እንወቅበት ሁላችን፣
እንድንሄድ ወደ አገራችን።
አገራችን የት ነው ለሚሉ፣
መሠረታዊውን ላላሟሉ።
ነግሮናል መምህራችን፣
ጳውሎስ ሐዋርያው አባታችን።
አገራችን በሰማይ ነው፣
ዜግነታችንም እዛው ነው።
እያለ የሰበከልን፣
የጌታን ወንጌል ያስተማረን።
ያመላከተን መንገዱን፣
ጌታ የተለመውን።

                        ነጋ ዓለማየሁ (12/16/2012)