አንድ ትልቅ ሰው ነበሩ አሉ። እኚህ ሰው በስተመጨረሻ ዘመናቸው አንድ ትልቅ ነገር ተገለጠላቸውና ለሌላው ትምህርት ይሆን ዘንድ ታሪካቸውን ተናገሩ። ነገሩ እንዲህ ነው። ሰውየው በልጅነት ዘመናቸው በጣም ታላቅ ነገር ያስባሉ። ይኸውም ዓለምን መቀየር ነበር። በመሆኑም ዓለምን መቀየር አለብኝ ብለው ተነሱ። ከዚያም ውለው አድረው ሲመለከቱት ዓለም በጣም ትልቅ በመሆኑ አገሬን ብቀይር መልካም ነው ብለው ተነሱ። ከዚያም ውለው አድረው ሲያስቡት አገር ትልቅ ነው። ስለዚህ ያለሁበት ክፍለ ግዛት መቀየር አለብኝ አሉ። ከዚያም ይህም አደከማቸውና ያለሁበትን አካባቢ ብቀይር ይሻላል አሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እድሜ እየጨመረ ቤተሰብም ተመስርቶ ከእውነታውም እየተማሩ ነው። በኋላም ይህ ሁሉ አይቻልም የራሴን ቤተሰብ ብቻ ብቀይር ትልቅ ነገር አደረኩ ማለት ነው ብለው ቤተሰባቸውን ለመቀየር ቆርጠው ተነሱ። የሚገርመው ነገር ያም አልሆን አለና ብዙ ሙከራ አድርገው ጊዜው ካለፈ በኋላ በስተመጨረሻ ብልጭ ያላበቸው ነገር “መለወጥ የምችለው ራሴን ብቻ ነው” አሉ። “ይንን ቀደም ብዬ ባውቅ ኑሮ እውነትም ሌሎችንም ላነሳሳ አርአያም ልሆናቸው እችል ነበር። እኔ ስለወጥ ዓለምም ይለወጣል” ብለው ደመደሙ።
ራስን መግዛት ቀላል ነገር አይደለም። በዘመናችን ራሳችን መግዛት አቅቶን ሌሎችን ግን ለመግዛት ብዙ እንጥራለን። ያ ባለመሆኑም ስንናደድ በራሳችን ጤና ላይ ችግር ስንፈጥር እንገኛለን። ራሱን በሚገባ የገዛ ሰው በሌሎች ላይ ለመንገሥ ብዙ ችግር የለበትም። በምሳሌነት መምራት ማለትም ይኸው ነው። የስሜት ሕዋሳቶች የሚያመጡትን ነገር ያለምንም ማጣራት ከተጠቀምንባቸው የስሜት ተገዢ እንጂ ስሜታችን የገዛን ወይም በራሳችን ላይ የነገሥን አይደለንም። ለምሳሌ ብንወስድ ዓይን የውጪውን ነገር ያያል፣ በማየቱም አእምሮአችንም ቀደም ሲል ከነበረው መረጃ ጋር ያገናዝብና ወደ አንድ ነገር ወደ ማድረግ ፍላጎት ይሄዳል። በዚያ ወቅት ራስን መግዛት የተላበሰ ሰው ዓይንን እንደ ሠራተኛ (Subject) በመቁጠር እንጂ እንደ ውሳኔ ሰጪ ባለመቁጠር ሕሊና የሚለውን ማድረግ ይችላል። እንዲሁም ሌሎች የስሜት ሕዋሳቶች የሚያመጡትን የፍላጎት ምንጭ የሚሆኑትን መረጃዎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀመ ራስን በመግዛት አኳኋን ውሳኔ ይሰጣል። ንጉሡ ሕሊና ይሆናል ማለት ነው። የስሜት ሕዋሳትም ለንጉሡ የሚያገለግሉ ሚኒስትሮች ይሆናሉ።
ራሱን የሚገዛ ሰው አፍንጫ ያሸተተውን፣ ጀሮ የሰማውን፣ ዓይን ያየውን፣ ጣትም የዳሰሰውን፣ ምላስም የቀመሰውን ወይም አእምሮ ያሰበውን ሁሉ አያደርግም። እነዚህን የሥራ ክፍሎች በሚገባ ይጠቀምባቸዋል። ሆኖም ግን ውሳኔ የሚሰጠው በስሜት ተኮር ሳይሆን በእሴት ተኮር ላይ ተመርኩዞ ነው። ሰዎች በመሆናችን ከእንስሶች የምንለይበት ዋናው ምክንያት የስሜት ተገዢ አለመሆናችን ነው። ራስን መግዛት ለብዙዎች የሕይዎት ዘመን ጉዞ ነው። አንዳንዶች ራስን የመግዛት ሐሳቡ እንዲሳካላቸው ስሜታዊ ሊያደርጋቸው ከሚችል ነገር ራሳቸውን ያገላሉ። ራሳቸውን አግልለውም ከአምላካቸው ጋር ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። ትልቁ ነገር ግን ራስን መግዛት ቀላል አለመሆኑን መረዳቱ ነው። ሌላውን ሰው “መግዛት” ይቻል ይሆናል። ለምሳሌ አምባገነን መንግሥታት በሌላው ላይ ነግሠው አገር አስተዳደርን ይላሉ። የሚገርመው ግን ሚሊዮኖችን ገዛን እያሉ ራሳቸውን መግዛት አለመቻላቸው ነው። ራሳቸውን መግዛት ቢችሉ የአምባ ገነንነት ባህሪ አይኖራቸውም ነበር።
ራስን መግዛት ከየትም የሚመጣ ሳይሆን ከመንፈሳዊነት የሚመነጭ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በላከላቸው መልዕክቱ 5:22 ላይ የመንፈስ ፍሬ ብሎ ካስቀመጣቸው ውስጥ “ራስን መግዛት” አንዱ የሆነው። መንፈሳዊ ሆኖ ፍሬ ማፍራት የግድ ነው። መቸም ገበሬ የዘራውን ለመሰብሰብ በየጊዜው ማሳውን፣ ያፈራውንና ሊያፈራ የጀመረውን እንደሚያይና እንደሚንከባከብ ሁሉ ማንኛውም ሐይማኖተኛ በአንድ በኩል ፍሬ የሚያፈራበትን ነገር ማመቻቸትና አስፈላጊውን መፈጸም ሲያስፈልግ በሌላ በኩል ደግሞ የመንፈሳዊነት ፍሬ ማፍራቱን መከታተል አስፈላጊ ነው። እያወቁ ጥረት (Conscious effort) ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት አንዳንዶቹ የሕይዎት ዘመን ጥረት ያደርጋሉ። መንፈሳዊ ስንሆን መንፈስን ወይም ዘላለማዊነትን እናስታውሳለን። ዘላለማዊነትን ወይም ሕያውነትን ስንረዳና ሕያው ለመሆን ስንነሳ ደግሞ የእግዚአብሔር የሆነውን እናደርጋለን እሱንም እንመስላለን። ራሳችን ገዝተን በጊዜያዊ በሚጠፋ ስሜት ሳይሆን ዘላለማዊነትን ተላብሰን ስንኖር በትክክልም ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚያስተምረን የዚህ ዓለም ሰዎች ሳንሆን የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች እንሆናለን ማለት ነው። ያ ማለት ደስታችን በዚህ አለም ይዞታችን ላይ ወይም በስሜት ሕዋሳቶቻችን ፍላጎት መሟላት ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን በራሳችን ላይ በመንገሣችን ይሆናል ማለት ነው።
.... ይቀጥላል