ከነጋ ዓለማየሁ (November 19, 2011)
“እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” (ዕብራውያን 12: 1-2)
ለመታገሥ ጽኑ ዓላማ ያስፈልጋል። ዓላማ ያላነገበ ሰው ትዕግሥት ከንቱ ይሆንበታል። አንድ የጦር መሪ እና ተራ ተዋጊ ወታደር ትልቅ ልዩነት አላቸው። ወታደሩ ከፊቱ የሚያገኘውን “ጠላት” በተባለው ሁሉ እርምጃ ለመውሰድ ወይም ለመተኮስ ይቸኩላል የጦር መሪው ደግሞ ከአጠቃላዩ ስኬት ወይም ድል ጋር በማገናኘት ወይም በማገናዘብ መወሰድ ያለበትን እርምጃ ይወስናል። በአብዛኛው ግን የጥቃት እርምጃ ላይ አይቸኩልም፤ መታገሥን ይመርጣል። ይህም የሚሆንበት እያንዳንዷ እርምጃ ከዋናው ለመጨረሻው ድል ታቀርበናለች ወይስ ታርቀናለች ብሎ በማሰብ ነው። የጠላት ኃይል ምንም እንኳ ጥቃትን ቢያደርስም ከመጨረሻው የግብ አቅጣጫ ጋር በማገናዘብ መታገሥን ይመርጣል። ይህ የሚሆነው መዳረሻውን የሚያውቅ መሪ ሲሆንና እንደሚደርስም ሲያምን ነው።
በመግቢያ ላይ የተጠቀሱት ከዕብራውያን 12:1-2 የተወሰዱት ጥቅሶች የሚያመለክቱት ይህንን ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያንን ሁሉ የደረሰበትን መከራ የቻለበትና ነውር የናቀበት ዋናው ምክንያት በእግዚአብሔር ዙፋን በቀኝ እንደሚቀመጥ በማወቁ ነው። የመከራው ብዛት የሰው ልጆች የፈጸሙትን ሐጢያት የሚያሳይ ሲሆን የእርሱ መታገሥ ግን ለማዳን የመጣ በመሆኑና ወደነበረበት ቦታ በክብር መመለስ ስላለበት የሆነ ነው።
በዛሬ ዘመን መታገሥ ሞኝነት ይመስላል። ሞኞችም የጠፉ ይመስላሉ። ሰዎች መታገስ እያቃተንም ብዙ ቁምነገር ያላቸው ነገሮች ቤተሰብንም ሆነ ማህበረሰብን ብሎም አገርን ሊጠቅሙ የሚችሉ ጉዳዮች ሲበላሹ እናያለን። ይህም ሊሆን የቻለበት ከአሰባሰበን ጉዳይ ይልቅ ወይም ከትልቁ ዓላማ ይልቅ እያንዳንዳችን ተልቀን እንገኝና የተለያዩ አመለካከቶችን ማስተናገድ ባለመቻላችን ትንንሽ ውጣ ውረዶችን መታገሥ ባለመቻላችን ዓላማችን ሳናሳካ እንበታተናለን።
ቤተሰብ ለምን ተመሠረተ? እኔስ ለምን ቤተሰብ መሠረትኩ? ዓላማው ምንድን ነው? እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ የመለሰ ቤተሰብ ተፋቅሮ፣ ተከባብሮና ተግባብቶ የመኖር እድሉ ሰፊ ነው። ቤተሰብ የተመሠረተበት ዓላማ የጊዜ ገደብ የለውም። የእድሜ ልክ ዓላማ ነው። ያ በመሆኑ በአንድ ጣራ ሥር የሚኖሩ ሰዎች አንድ የሚያደርጋቸው የቤቱ ጣራ ሳይሆን መሆን ያለበት ያገናኛቸው ዓላማ ነው። ዓላማ አንድ ካደረጋቸው የቤቱ ግድግዳም ሆነ ጣራ ባይኖር በአንድ ላይ ተያይዘው ይገኛሉ። በዛሬው ዓለም የቤቱ ጣሪያ አስገድዶ በአንድ ላይ የሚያኖራቸው ቤተሰቦች ቁጥር በጣም ብዙ ነው። አንድንዶቹ ቤታቸውም ሰፊ በመሆኑና ብዙ ክፍሎች ስለሚኖሩት ምንም እንኳ ለውጭ ሰው በአንድ ቤት በመኖራቸው በአንድ ላይ የሚኖሩ ቢመስሉም መኝታ ለይተው ይኖራሉ። እንግዲህ በአንድ ጣራ ሥር የተለያዬ ክፍል ማለት ነው። ይህን ምን አመጣው ብንል መጀመሪያውኑ አንድ ጣራ ሥር የመጡበትና ምክንያትና ዓላም ረስተውታል ማለት ነው።
ክርስቲያን ለሆነ ቤተሰብ እግዚአብሔር የመሠረተው ተቋም በመሆኑ ያንን የእግዚአብሔርን ዓላማ እያሰቡ በትዕግሥት ይኖራሉ። ትዕግሥት የሚያስፈልገውም አንዳንዴ ለሚፈጠር የሕይወት ውጣ ውረድ ነው። ውጣ ውረዱ ያለና የነበረ ወደ ፊትም የሚኖር መሆኑን ይረዳሉ። የማይፈተን እድገት የለውም። ውጣ ውረዱ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመድረስ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ይረዳሉ። ጎበዝ ተማሪ ፈተና አይፈራም። ለምን ቢባል ፈታናውን አልፎ ወደሚቀጥለው ክፍል እንደሚያልፍ ስለሚገነዘብ ነው። ስለዚህ ችግርን መታገሥ፣ እለታዊ ስሜትን ሳይሆን ዘላቂ ዓላማን መሠረት በማድረግ ውሳኔ መስጠት ለጥሩ ውጤት ያበቃል።
አገርን እንመራለን ብለው የሚደረጁትም ብዙ ጊዜ ሲፈርሱ አይተናል። እኔ በዚህ ውስጥ ለነበሩ የምጠይቀው ጥያቄ ቢኖር “ለምን ጀመራችሁ ለምንስ ታፈርሳላችሁ?” መቸም ይብዙዎችን መልስ ስንሰማው የተለመደው እጣትን በሌላው ላይ መቀሰር ነው። እጣት የሚቀሰርበትንስ እንዴት መታገሥ አልቻሉም? እኔ እንደማስበው አንድ ላይ እንዲመጡ ያደረጋችውን ትልቁን ዓላማ ካልረሱት በስተቀር መታገሥ አይቸግራቸውም። ዋናው ዓላማ ከተረሳ ግን ዓላማውን ለማስፈጸም የሚቀረጸው ስትራተጂ የአለመግባባት ምንጭ ይሆንና ዋናው ነገር ተረስቶ ይቀራል። ዋናው ዓላማ ካልተረሳ ግን ማንኛውም ዓላማውን ለማሳካት የሚመጣ ሐሳብ ሁሉ ልንቀበለው የግድ ይሆናል። ማንም ያመንጨው ማንም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆን የለበትም። ዋናው ነገር ከግባችን ለመድረስ ይረዳናል ወይስ አይረዳንም ነው መሆን ያለበት።
ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ረጂም ጊዜ ይወስዳል። ይህ ረጂም ጊዜ የሚወስድ ነገር በዋናነት ትዕግሥትን ይፈልጋል። እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር ወጥተው ወደ ቃል ኪዳኗ መሬት ለመግባት 40 ዓመታት ተጉዘዋል። በዚህ ትዕግሥት አስጨራሺ ጉዞ ብዙዎቹ አልደረሱም። የታገሱትና እንገባለን ብለው ያመኑት ግን ደርሰዋል። ትዕግሥት ዓላማን ማወቅና ይሆናል ብሎ ማመንን ይጠይቃልና ነው። ስለዚህ መታገሥ የሚያስቸለን ዋናው ነገር የምንታገሠው ለምንድን እንደሆነ ማወቁ ነው።
... ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment