Thursday, November 10, 2011

ትዕግሥት ለምን ያስፈልጋል?

በዘመናችን አንድን ነገር ለማግኘት በችኮላ መፈለግ ወይም በፍጥነት መድረስ ወይም መፈጸም አለበት የሚል አስተሳሰብ በሰፊው ይንጸባረቃል። ልጆች አንድ ነገር ጠይቀው ወዲያውኑ ካላገኙ የቤቱን ሰላም ይፈታተናሉ። ልጆች ብቻም ሳይሆኑ ታላላቆችም ቢሆን አንድን ነገር በመታገሥ መጠበቅ አስቸጋሪ ሆኗል። እውነታው ግን ሁሉም ነገር የሁነታ ጊዜ አለው። የሰው ልጅ ጽንስ ተረግዞ ልጅ ሆኖ እስከሚወለድ የ9 ወር ጊዜ ያስፈልጋል። በመሆኑም አንድ ሰው ተነስቶ  ልጅ እፈልጋለሁና አሁንኑ ይድረስ ብሎ ማሰብ አይችልም ካሰበም የጤና ችግር አለባቸው ከሚባሉ ሰዎች አንዱ ይሆናል ማለት ነው። መስከረም አልቆ ሌላ መስከረም እስኪመጣ 11 ወራት መቆጠር አለበት። ምግብም የመብሰያ ጊዜውን ጠብቆ መብሰል አለበት። ያ ሊሆን ካልቻለ ያለጊዜው ሳይበስል የተበላ ምግብ ለጤና ተስማሚም አይሆንም።  
        በችኮላ መፍትሔ ተብሎ የተወሰደ ነገር ሁሉ በአብዛኛው ትክክለኛ መፍትሔ አይደለም። አባቶቻችን ሲተርቱ “የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ” ይላሉ። በመሆኑም ትዕግሥት የአንድን ነገር የሁነታ ጊዜ እንዳለው በመረዳት መጠበቅ የግድ ይሆናል። ጥበቃው ታዲያ እምነትም ያስፈልገዋል። ይሆናል ብሎ ለመሆኑ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው። ትዕግሥትን በሚገባ ተረድተን ስንታገስ በየጊዜው የሚገጥመን ነገር ስሜትን የሚጎዳ አይሆንም። ያሰብነው ነገር ሳይሳካ ቢቀር ወይም ካሰብነው ጊዜ ውጭ ቢራዘም አሁንም በጠቢቡ ሰለሞን አድሮ “ለሁሉም ጊዜ አለው” ያለንን እግዚአብሔርን እናስታውሳለን ተስፋም እናደርጋለን። የትዕግሥት አስፈላጊነትም ይህንን እውነታ እንድንረዳ ነው። አንድ ሰው አንድ የማይፈለግ ጸባይ ቢኖረው ያንን ጸባዩን ለመቀየር ትልቅ ትዕግሥት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ ያንን መልካም ያልሆነውን ጸባዩን ለመያዝ ጊዜ ወስዶበታል። ታዲያ ጊዜ ወስዶ ያጠራቀመውን ነገር በአንድ አፍታ ሊቀይረው አይችልም። እሱ እራሱም ሆነ በዙሪያው የሚገኙት ሊታገሱ ይገባል።
እግዚአብሔርን ተስፋ አድረገው የተንቀሳቀሱ ሁሉ ታላቅ ትዕግሥት አሳይተዋል። እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በባርነት ከሚገዙበት ወጥተው ወደ ቃል ኪዳኗ መሬት ለመግባት 40 ዓመታት ወስዶባቸዋል። በዚህ በእስራኤላውያን የነፃነት ጉዞ የእግዚአብሔር እጅ ሆኖ ዋና ተዋናይ የነበረው ነቢዩ አባታችን ሙሴ ብዙ ነገሮች የገጠሙት ቢሆንም ሰዎቹን በትዕግሥት አስተዳድሯል። ምንም እንኳን ወደ ቃልኪዳኗ መሬት መግባት ባይችልም የነፃነት ጉዞው አውራ ተዋናይ በመሆን ይታወቃል።
እዮብ ከአብራኩ የወጡትን ልጆችና በዓለም ያፈራቸውን ህብቱንና ንብረቱን ሲያጣ ወደነበረበት ክብሩና የበለጠም ሀብት እንዲያገኝ ያደረገው ትዕግሥት የተባለው የመንፈስ ፍሬ ነው። ባለቤቱም ሆኑ የቅርብ ሰዎቹ የደረሰበት ነገር ከባድ መሆኑን ነግረው እግዚአብሔርን ማምለኩን እንዲያቆም ለማሳመን ሲሞክሩ በእምቢተኝነት እንዲቆይ ያደረገው ትዕግሥት ነው። አሁን ባለንበት ዘመንም መታገሥ የቻለ ረጅም መንገድ መሄድን ይመርጣል የተሻለ ቦታም ይደርሳል። ረጅም መንገድ የሚሄዱም በመንገድ ብዙ ችግሮች ይገጥሙአቸዋል። ሆኖም ግን በትዕግሥት ካሳለፉት ቀደም ሲል ካሰቡት መድረሻቸው ሲደርሱ ፍሬው ያስደስታቸዋል። የታመመ ሰው እድናለሁ ወይም ወደ አምላኬ እሄዳለሁ የሚለውን በማመን ታጋሽ ከሆነ በህመሙ አይሰቃይም። እንዲያውም በአካባብው የሉትን ሰዎች የሚያረጋጋ ይሆናል።

... ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment