Monday, November 21, 2011

ራስን መግዛት

አንድ  ትልቅ ሰው ነበሩ አሉ። እኚህ ሰው በስተመጨረሻ  ዘመናቸው አንድ ትልቅ ነገር ተገለጠላቸውና ለሌላው ትምህርት ይሆን ዘንድ ታሪካቸውን ተናገሩ። ነገሩ እንዲህ ነው። ሰውየው በልጅነት ዘመናቸው በጣም ታላቅ ነገር ያስባሉ። ይኸውም ዓለምን መቀየር ነበር። በመሆኑም ዓለምን መቀየር አለብኝ ብለው ተነሱ። ከዚያም ውለው አድረው ሲመለከቱት ዓለም በጣም ትልቅ በመሆኑ አገሬን ብቀይር መልካም ነው ብለው ተነሱ። ከዚያም ውለው አድረው ሲያስቡት አገር ትልቅ ነው። ስለዚህ ያለሁበት ክፍለ ግዛት መቀየር አለብኝ አሉ። ከዚያም ይህም አደከማቸውና ያለሁበትን አካባቢ ብቀይር ይሻላል አሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እድሜ  እየጨመረ ቤተሰብም ተመስርቶ ከእውነታውም እየተማሩ ነው። በኋላም ይህ ሁሉ አይቻልም የራሴን ቤተሰብ ብቻ ብቀይር ትልቅ ነገር አደረኩ ማለት ነው ብለው ቤተሰባቸውን ለመቀየር ቆርጠው ተነሱ። የሚገርመው ነገር ያም አልሆን አለና ብዙ ሙከራ አድርገው ጊዜው ካለፈ በኋላ በስተመጨረሻ ብልጭ ያላበቸው ነገር “መለወጥ የምችለው ራሴን ብቻ ነው” አሉ። “ይንን ቀደም ብዬ ባውቅ ኑሮ  እውነትም ሌሎችንም ላነሳሳ አርአያም ልሆናቸው እችል ነበር። እኔ ስለወጥ ዓለምም ይለወጣል” ብለው ደመደሙ። 

ራስን መግዛት ቀላል ነገር አይደለም። በዘመናችን ራሳችን መግዛት አቅቶን ሌሎችን ግን ለመግዛት ብዙ እንጥራለን። ያ ባለመሆኑም ስንናደድ በራሳችን ጤና  ላይ ችግር ስንፈጥር እንገኛለን። ራሱን በሚገባ  የገዛ ሰው በሌሎች ላይ ለመንገሥ ብዙ ችግር የለበትም። በምሳሌነት መምራት ማለትም ይኸው ነው። የስሜት ሕዋሳቶች የሚያመጡትን ነገር ያለምንም ማጣራት ከተጠቀምንባቸው የስሜት ተገዢ እንጂ ስሜታችን የገዛን ወይም በራሳችን ላይ የነገሥን አይደለንም። ለምሳሌ ብንወስድ ዓይን የውጪውን ነገር ያያል፣ በማየቱም አእምሮአችንም  ቀደም ሲል ከነበረው መረጃ  ጋር ያገናዝብና ወደ አንድ ነገር ወደ ማድረግ ፍላጎት ይሄዳል። በዚያ  ወቅት ራስን መግዛት የተላበሰ ሰው ዓይንን እንደ ሠራተኛ (Subject) በመቁጠር እንጂ እንደ ውሳኔ ሰጪ ባለመቁጠር ሕሊና የሚለውን ማድረግ ይችላል። እንዲሁም ሌሎች የስሜት ሕዋሳቶች የሚያመጡትን የፍላጎት ምንጭ የሚሆኑትን መረጃዎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀመ ራስን በመግዛት አኳኋን ውሳኔ  ይሰጣል። ንጉሡ ሕሊና ይሆናል ማለት ነው። የስሜት ሕዋሳትም ለንጉሡ የሚያገለግሉ ሚኒስትሮች ይሆናሉ።      

ራሱን የሚገዛ ሰው አፍንጫ ያሸተተውን፣ ጀሮ የሰማውን፣ ዓይን ያየውን፣ ጣትም የዳሰሰውን፣ ምላስም የቀመሰውን ወይም አእምሮ ያሰበውን ሁሉ አያደርግም። እነዚህን የሥራ ክፍሎች በሚገባ ይጠቀምባቸዋል። ሆኖም ግን ውሳኔ የሚሰጠው በስሜት ተኮር ሳይሆን በእሴት ተኮር ላይ ተመርኩዞ ነው። ሰዎች በመሆናችን ከእንስሶች የምንለይበት ዋናው ምክንያት የስሜት ተገዢ አለመሆናችን ነው። ራስን መግዛት ለብዙዎች የሕይዎት ዘመን ጉዞ ነው። አንዳንዶች ራስን የመግዛት ሐሳቡ እንዲሳካላቸው ስሜታዊ ሊያደርጋቸው ከሚችል ነገር ራሳቸውን ያገላሉ። ራሳቸውን አግልለውም ከአምላካቸው ጋር ብዙ ጊዜ  ያሳልፋሉ። ትልቁ ነገር ግን ራስን መግዛት ቀላል አለመሆኑን መረዳቱ ነው። ሌላውን ሰው “መግዛት” ይቻል ይሆናል። ለምሳሌ አምባገነን መንግሥታት በሌላው ላይ ነግሠው አገር አስተዳደርን ይላሉ። የሚገርመው ግን ሚሊዮኖችን ገዛን እያሉ ራሳቸውን መግዛት አለመቻላቸው ነው። ራሳቸውን መግዛት ቢችሉ የአምባ ገነንነት ባህሪ አይኖራቸውም ነበር።

ራስን መግዛት ከየትም የሚመጣ  ሳይሆን ከመንፈሳዊነት የሚመነጭ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በላከላቸው መልዕክቱ 5:22 ላይ የመንፈስ ፍሬ ብሎ ካስቀመጣቸው ውስጥ “ራስን መግዛት” አንዱ የሆነው። መንፈሳዊ ሆኖ ፍሬ ማፍራት የግድ ነው። መቸም ገበሬ የዘራውን ለመሰብሰብ በየጊዜው ማሳውን፣ ያፈራውንና ሊያፈራ የጀመረውን እንደሚያይና እንደሚንከባከብ ሁሉ ማንኛውም ሐይማኖተኛ በአንድ በኩል ፍሬ የሚያፈራበትን ነገር ማመቻቸትና አስፈላጊውን መፈጸም ሲያስፈልግ በሌላ በኩል ደግሞ የመንፈሳዊነት ፍሬ ማፍራቱን መከታተል አስፈላጊ ነው። እያወቁ ጥረት (Conscious effort) ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት አንዳንዶቹ የሕይዎት ዘመን ጥረት ያደርጋሉ። መንፈሳዊ ስንሆን መንፈስን ወይም ዘላለማዊነትን እናስታውሳለን። ዘላለማዊነትን ወይም ሕያውነትን ስንረዳና ሕያው ለመሆን ስንነሳ ደግሞ  የእግዚአብሔር የሆነውን እናደርጋለን እሱንም እንመስላለን። ራሳችን ገዝተን በጊዜያዊ በሚጠፋ ስሜት ሳይሆን ዘላለማዊነትን ተላብሰን ስንኖር በትክክልም ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚያስተምረን የዚህ ዓለም ሰዎች ሳንሆን የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች እንሆናለን ማለት ነው። ያ ማለት ደስታችን በዚህ አለም ይዞታችን ላይ ወይም በስሜት ሕዋሳቶቻችን ፍላጎት መሟላት ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን በራሳችን ላይ በመንገሣችን ይሆናል ማለት ነው።

.... ይቀጥላል

Saturday, November 19, 2011

የሚፈታተነንን ወይም ጊዜ የሚውስድን እንዴት ልንታገሥ እንችላለን?

ከነጋ ዓለማየሁ (November 19, 2011)

እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” (ዕብራውያን 12: 1-2)
ለመታገሥ ጽኑ ዓላማ ያስፈልጋል። ዓላማ ያላነገበ ሰው ትዕግሥት ከንቱ ይሆንበታል። አንድ የጦር መሪ እና ተራ ተዋጊ ወታደር ትልቅ ልዩነት አላቸው። ወታደሩ ከፊቱ የሚያገኘውን “ጠላት” በተባለው ሁሉ እርምጃ  ለመውሰድ ወይም ለመተኮስ ይቸኩላል የጦር መሪው ደግሞ ከአጠቃላዩ ስኬት ወይም ድል ጋር በማገናኘት ወይም በማገናዘብ መወሰድ ያለበትን እርምጃ ይወስናል። በአብዛኛው ግን የጥቃት እርምጃ ላይ አይቸኩልም፤ መታገሥን ይመርጣል። ይህም የሚሆንበት እያንዳንዷ  እርምጃ ከዋናው ለመጨረሻው ድል ታቀርበናለች ወይስ ታርቀናለች ብሎ በማሰብ ነው። የጠላት ኃይል ምንም እንኳ ጥቃትን ቢያደርስም ከመጨረሻው የግብ አቅጣጫ ጋር በማገናዘብ መታገሥን ይመርጣል። ይህ የሚሆነው መዳረሻውን የሚያውቅ መሪ ሲሆንና እንደሚደርስም ሲያምን ነው።  

በመግቢያ ላይ የተጠቀሱት ከዕብራውያን 12:1-2 የተወሰዱት ጥቅሶች የሚያመለክቱት ይህንን ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያንን ሁሉ የደረሰበትን መከራ የቻለበትና ነውር የናቀበት ዋናው ምክንያት በእግዚአብሔር ዙፋን በቀኝ እንደሚቀመጥ በማወቁ ነው። የመከራው ብዛት የሰው ልጆች የፈጸሙትን ሐጢያት የሚያሳይ ሲሆን የእርሱ መታገሥ ግን ለማዳን የመጣ በመሆኑና ወደነበረበት ቦታ በክብር መመለስ ስላለበት የሆነ ነው።

በዛሬ ዘመን መታገሥ ሞኝነት ይመስላል። ሞኞችም የጠፉ ይመስላሉ። ሰዎች መታገስ እያቃተንም ብዙ ቁምነገር ያላቸው ነገሮች ቤተሰብንም ሆነ ማህበረሰብን ብሎም አገርን ሊጠቅሙ የሚችሉ ጉዳዮች ሲበላሹ እናያለን። ይህም ሊሆን የቻለበት ከአሰባሰበን ጉዳይ ይልቅ ወይም ከትልቁ ዓላማ ይልቅ እያንዳንዳችን ተልቀን እንገኝና የተለያዩ  አመለካከቶችን ማስተናገድ ባለመቻላችን ትንንሽ ውጣ ውረዶችን መታገሥ ባለመቻላችን ዓላማችን ሳናሳካ እንበታተናለን።

ቤተሰብ ለምን ተመሠረተ? እኔስ ለምን ቤተሰብ መሠረትኩ? ዓላማው ምንድን ነው? እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ የመለሰ ቤተሰብ ተፋቅሮ፣ ተከባብሮና ተግባብቶ የመኖር እድሉ ሰፊ ነው። ቤተሰብ የተመሠረተበት ዓላማ የጊዜ ገደብ የለውም። የእድሜ ልክ ዓላማ ነው። ያ በመሆኑ በአንድ ጣራ ሥር የሚኖሩ ሰዎች አንድ የሚያደርጋቸው የቤቱ ጣራ ሳይሆን መሆን ያለበት ያገናኛቸው ዓላማ  ነው። ዓላማ አንድ ካደረጋቸው የቤቱ ግድግዳም ሆነ ጣራ ባይኖር በአንድ ላይ ተያይዘው ይገኛሉ። በዛሬው ዓለም የቤቱ ጣሪያ አስገድዶ በአንድ ላይ የሚያኖራቸው ቤተሰቦች ቁጥር በጣም ብዙ ነው። አንድንዶቹ ቤታቸውም ሰፊ በመሆኑና ብዙ ክፍሎች ስለሚኖሩት ምንም እንኳ ለውጭ ሰው በአንድ ቤት በመኖራቸው በአንድ ላይ የሚኖሩ ቢመስሉም መኝታ ለይተው ይኖራሉ። እንግዲህ በአንድ ጣራ ሥር የተለያዬ ክፍል ማለት ነው። ይህን ምን አመጣው ብንል መጀመሪያውኑ አንድ ጣራ  ሥር የመጡበትና ምክንያትና ዓላም ረስተውታል ማለት ነው።

ክርስቲያን ለሆነ ቤተሰብ እግዚአብሔር የመሠረተው ተቋም በመሆኑ ያንን የእግዚአብሔርን ዓላማ እያሰቡ በትዕግሥት ይኖራሉ። ትዕግሥት የሚያስፈልገውም አንዳንዴ ለሚፈጠር የሕይወት ውጣ ውረድ ነው። ውጣ ውረዱ ያለና የነበረ  ወደ ፊትም የሚኖር መሆኑን  ይረዳሉ። የማይፈተን እድገት የለውም። ውጣ ውረዱ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመድረስ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ይረዳሉ። ጎበዝ ተማሪ ፈተና  አይፈራም። ለምን ቢባል ፈታናውን አልፎ  ወደሚቀጥለው ክፍል እንደሚያልፍ ስለሚገነዘብ ነው። ስለዚህ ችግርን መታገሥ፣ እለታዊ ስሜትን ሳይሆን ዘላቂ ዓላማን መሠረት በማድረግ ውሳኔ  መስጠት ለጥሩ ውጤት ያበቃል።  

አገርን እንመራለን ብለው የሚደረጁትም ብዙ ጊዜ ሲፈርሱ አይተናል። እኔ በዚህ ውስጥ ለነበሩ የምጠይቀው ጥያቄ ቢኖር “ለምን ጀመራችሁ ለምንስ ታፈርሳላችሁ?” መቸም ይብዙዎችን መልስ ስንሰማው የተለመደው እጣትን በሌላው ላይ መቀሰር ነው። እጣት የሚቀሰርበትንስ እንዴት መታገሥ አልቻሉም? እኔ እንደማስበው አንድ ላይ እንዲመጡ ያደረጋችውን ትልቁን ዓላማ ካልረሱት በስተቀር መታገሥ አይቸግራቸውም። ዋናው ዓላማ ከተረሳ ግን ዓላማውን ለማስፈጸም የሚቀረጸው ስትራተጂ የአለመግባባት ምንጭ ይሆንና ዋናው ነገር ተረስቶ ይቀራል። ዋናው ዓላማ ካልተረሳ  ግን ማንኛውም ዓላማውን ለማሳካት የሚመጣ ሐሳብ ሁሉ ልንቀበለው የግድ ይሆናል። ማንም ያመንጨው ማንም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆን የለበትም። ዋናው ነገር ከግባችን ለመድረስ ይረዳናል ወይስ አይረዳንም ነው መሆን ያለበት።

ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ረጂም ጊዜ ይወስዳል። ይህ ረጂም ጊዜ የሚወስድ ነገር በዋናነት ትዕግሥትን ይፈልጋል። እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር ወጥተው ወደ  ቃል ኪዳኗ መሬት ለመግባት 40 ዓመታት ተጉዘዋል። በዚህ ትዕግሥት አስጨራሺ ጉዞ ብዙዎቹ አልደረሱም። የታገሱትና እንገባለን ብለው ያመኑት ግን ደርሰዋል። ትዕግሥት ዓላማን ማወቅና ይሆናል ብሎ ማመንን ይጠይቃልና ነው። ስለዚህ መታገሥ የሚያስቸለን ዋናው ነገር የምንታገሠው ለምንድን እንደሆነ  ማወቁ ነው።

... ይቀጥላል

Thursday, November 10, 2011

ትዕግሥት ለምን ያስፈልጋል?

በዘመናችን አንድን ነገር ለማግኘት በችኮላ መፈለግ ወይም በፍጥነት መድረስ ወይም መፈጸም አለበት የሚል አስተሳሰብ በሰፊው ይንጸባረቃል። ልጆች አንድ ነገር ጠይቀው ወዲያውኑ ካላገኙ የቤቱን ሰላም ይፈታተናሉ። ልጆች ብቻም ሳይሆኑ ታላላቆችም ቢሆን አንድን ነገር በመታገሥ መጠበቅ አስቸጋሪ ሆኗል። እውነታው ግን ሁሉም ነገር የሁነታ ጊዜ አለው። የሰው ልጅ ጽንስ ተረግዞ ልጅ ሆኖ እስከሚወለድ የ9 ወር ጊዜ ያስፈልጋል። በመሆኑም አንድ ሰው ተነስቶ  ልጅ እፈልጋለሁና አሁንኑ ይድረስ ብሎ ማሰብ አይችልም ካሰበም የጤና ችግር አለባቸው ከሚባሉ ሰዎች አንዱ ይሆናል ማለት ነው። መስከረም አልቆ ሌላ መስከረም እስኪመጣ 11 ወራት መቆጠር አለበት። ምግብም የመብሰያ ጊዜውን ጠብቆ መብሰል አለበት። ያ ሊሆን ካልቻለ ያለጊዜው ሳይበስል የተበላ ምግብ ለጤና ተስማሚም አይሆንም።  
        በችኮላ መፍትሔ ተብሎ የተወሰደ ነገር ሁሉ በአብዛኛው ትክክለኛ መፍትሔ አይደለም። አባቶቻችን ሲተርቱ “የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ” ይላሉ። በመሆኑም ትዕግሥት የአንድን ነገር የሁነታ ጊዜ እንዳለው በመረዳት መጠበቅ የግድ ይሆናል። ጥበቃው ታዲያ እምነትም ያስፈልገዋል። ይሆናል ብሎ ለመሆኑ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማመቻቸት አስፈላጊ ነው። ትዕግሥትን በሚገባ ተረድተን ስንታገስ በየጊዜው የሚገጥመን ነገር ስሜትን የሚጎዳ አይሆንም። ያሰብነው ነገር ሳይሳካ ቢቀር ወይም ካሰብነው ጊዜ ውጭ ቢራዘም አሁንም በጠቢቡ ሰለሞን አድሮ “ለሁሉም ጊዜ አለው” ያለንን እግዚአብሔርን እናስታውሳለን ተስፋም እናደርጋለን። የትዕግሥት አስፈላጊነትም ይህንን እውነታ እንድንረዳ ነው። አንድ ሰው አንድ የማይፈለግ ጸባይ ቢኖረው ያንን ጸባዩን ለመቀየር ትልቅ ትዕግሥት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ ያንን መልካም ያልሆነውን ጸባዩን ለመያዝ ጊዜ ወስዶበታል። ታዲያ ጊዜ ወስዶ ያጠራቀመውን ነገር በአንድ አፍታ ሊቀይረው አይችልም። እሱ እራሱም ሆነ በዙሪያው የሚገኙት ሊታገሱ ይገባል።
እግዚአብሔርን ተስፋ አድረገው የተንቀሳቀሱ ሁሉ ታላቅ ትዕግሥት አሳይተዋል። እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በባርነት ከሚገዙበት ወጥተው ወደ ቃል ኪዳኗ መሬት ለመግባት 40 ዓመታት ወስዶባቸዋል። በዚህ በእስራኤላውያን የነፃነት ጉዞ የእግዚአብሔር እጅ ሆኖ ዋና ተዋናይ የነበረው ነቢዩ አባታችን ሙሴ ብዙ ነገሮች የገጠሙት ቢሆንም ሰዎቹን በትዕግሥት አስተዳድሯል። ምንም እንኳን ወደ ቃልኪዳኗ መሬት መግባት ባይችልም የነፃነት ጉዞው አውራ ተዋናይ በመሆን ይታወቃል።
እዮብ ከአብራኩ የወጡትን ልጆችና በዓለም ያፈራቸውን ህብቱንና ንብረቱን ሲያጣ ወደነበረበት ክብሩና የበለጠም ሀብት እንዲያገኝ ያደረገው ትዕግሥት የተባለው የመንፈስ ፍሬ ነው። ባለቤቱም ሆኑ የቅርብ ሰዎቹ የደረሰበት ነገር ከባድ መሆኑን ነግረው እግዚአብሔርን ማምለኩን እንዲያቆም ለማሳመን ሲሞክሩ በእምቢተኝነት እንዲቆይ ያደረገው ትዕግሥት ነው። አሁን ባለንበት ዘመንም መታገሥ የቻለ ረጅም መንገድ መሄድን ይመርጣል የተሻለ ቦታም ይደርሳል። ረጅም መንገድ የሚሄዱም በመንገድ ብዙ ችግሮች ይገጥሙአቸዋል። ሆኖም ግን በትዕግሥት ካሳለፉት ቀደም ሲል ካሰቡት መድረሻቸው ሲደርሱ ፍሬው ያስደስታቸዋል። የታመመ ሰው እድናለሁ ወይም ወደ አምላኬ እሄዳለሁ የሚለውን በማመን ታጋሽ ከሆነ በህመሙ አይሰቃይም። እንዲያውም በአካባብው የሉትን ሰዎች የሚያረጋጋ ይሆናል።

... ይቀጥላል

Wednesday, November 9, 2011

ትዕግሥት


ት የውን ቃል ወይም ጽንሰ ሃሳብ በአብዛኛው የመንጠቀምበት ስሜታችን የሚፈታተኑ ነገሮችን ችሎ ከማለፍ ጋር በተያያዘ ነው። ለዚህም በተለምዶ

“መቻል ምን ይከፋል
ሆድ ከአገር ይሰፋል” ይባላል።

አንድን ነገር ታግሠን በማሳለፋችንም በአብዛኛው ደስተኞች እንሆናለን። ይህ አይነቱ መታገሥ በወቅቱ የባሰ ችግር እንዳይገጥም የሚጠቅም ሲሆን በችግሩ ዙሪያ ግን ዘለቄታዊ መፍትሄ ላያመጣ ይችላል። ት ስሜትን አምቆ መያዝ ሳይሆን የምንፈልገው ነገር ቀና በሆነ አስተሳሰብ ይሆናል ብሎ መጠበቅን ይመለከታል። ት ውጤቱ ብቻ ሳይሆን በትክክል ከታገን ሂደቱም አስደሳች ነው። በውስጥ “አንጀትን እያሳረሩ” ስለትት ማውራት ትዕግሥትን በሚገባ አለመረዳትን ከማመላከቱም በላይ ጎጂነቱ ስለሚያመዝን ሰዎች መታገስን እንደሞኝነት ሊቆጥሩት
ትዕግሥት ምንድን ነው?
በህይዎታችን መታገን የሚፈልጉ ብዙ ገጠመኞች አሉ። በዚህ ውስብስብ በሆነ ዓለም ውስጥ መታገሥ ወይም አለመታገሥ ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው። አንዳንዴ ት ሳይሆን ፍጥነት የሚያስፈልጋቸው ነገሮች አሉ። የአንድ ደቂቃ መዘግየት ይኸ ነው የማይባል የሕይዎት ዘመን ዕድል ሊያሳጣ ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ ለሴኮንዶች መታገሥ አለመቻል ለህልፈተ ሕይዎት ያደርሳል። ለምሳሌ ያህል መኪና የሚነዳ ሰው መታገሥ ባለመቻሉ ከፍተኛ አደጋ እንዲደርስ ያደርጋል። ይህ እንግዲህ ን ከጊዜ ጋር ስናየው የመታገሡ ሁኔታ ሳይሆን ጊዜ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ነው የምናየው። በአንድበኩል በመዘግየት ሊቀርብን የሚችል አጋጣሚ በሌላ በኩል ደግሞ በመቸኮል የሚደርስብን ጉዳት። የተረጋጋ ሕይዎት ያለው በብርሃን የሚኖር ይህንን መለየት ስለማይቸገር ሁለቱንም እንደሁኔታቸው ያከናውናል።
ይህንን ጽንሰ ሐሳብ ማለትም ከጊዜ ጋር የተያያዘውን ያመጣሁበት ምክንያት አንባቢዎቼ “መታገሥ ድርጊት አለመፈጸም ነው” ከሚለው ጋር እንዳያያይዙት ከመፈለግ ነው። እየሱስ ክርስቶስ ያንን ሁሉ መከራ በ ያሳለፈበት ምክንያት ውጤቱን በማወቁ ነው። ውጤቱም ለሰው ልጆች ድኅነትን ማምጣት፣ የእግዚአብሔርን ማንነት ማሳየት - ሙቶ ሌሎችን በማዳን። እንደዚህ አይነቱ ከፍተኛ ኃይል አለው። መታገሥ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፦
·         የቤተሰብ ግንኙነት የሰመረ ለመሆን
·         በሥራ ቦታ ከሥራ ባልደረቦች ጋር ያለ ግንኙነት አለማማር
·         ያለንበት የኢኮኖሚ ሁኔታ ዝቅተኝነት
·         በራሳችንም ሆነ  በምንወዳቸው ላይ የደረሰ የጤና ችግር
·         የምንወዳቸው ሰዎች ያሉበት ሁኔታ መልካም አለመሆንና የመሳሰሉት
·         በዓለም ላይ ያሉ ፍትሀዊ ያልሆኑ አሰራሮች
ባለት ዘመን የሚታዩ ክስተቶች ናቸው። እነዚህ ክስተቶችም እልህ አስጨራሾችና ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል። ሰዎች የችግራቸውን መፍትሔ የማግኛ ጊዜ ለማሳጠር መታገስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ይህንን ስል የችግሩ ባለቤቶች እጃቸውንና እግራቸውን አጣጥፈው ቁጭ ይላሉ ማለት አይደለም። ማድረግ ያለባቸውን ነገር መጫዎት ያለባቸውን ጨዋታ ማለትም የራሳቸውን ድርሻ መወጣት የግድ ነው። መታገስ ማለትም ውጤቱን ከመጠበቅ አንጻር እንጂ የራስን ድርሻ ለመፈጸም መታገስ ቦታ የለውም።
አንዳንድ ጊዜ ችግር ሲደርስ ከችግሩ በመሸሽ መፍትሔ ያገኘን ሊመስለን ይችላል። ሆኖም ግን ዘለቄታዊ መፍትሔ የምናገኘው ችግሩን በመግጠም ነው። ችግሩ በደረሰ ጊዜም ከችግሩ መሸሽ ሳይሆን በ መፍትሔ መፈለግ ጠቃሚ ነው። ጠቢቡ ሰለሞን የን ኃይል ሲገልጽትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ጸጥ ያደርጋልና የገዢ ቍጣ የተነሣብህ እንደ ሆነ ስፍራህን አትልቀቅ። (መክብብ 10:4) በበላይ አካል ቁጣ ተደናግጦ ቦታን መልቀቅ እንደማያስፈልግና በኃጢአት ላይ ምን ያህል ሃያል ስልጣን እንዳለው ያስረዳናል። ቦታውን ከለቀቅን የምናስበውን ነገር ተተነዋልና ሊደግፉን የሚያስቡ ሰዎች ካሉም ሀሳባችን መተዋችንን (መሸሻችንን) በማየት ሊዘረጉ ያሰቡትን የትብብር እጅ ይሰበስባሉ።
ከት ጋር ሁልጊዜ አብሮ የሚሄደው ቀና አስተሰሰብ ነው። ስንታገሥ ውጤቱ መልካም ይሆናል በሚል አስተሳሰብና ለቀናው ነገር መምጣት የበኩላችን አስተዋጽኦ በማድረግ መሆን አለበት። ጠማማው ይቃናል፣ የጎደለው ይሞላል፣ የተጣላው ይታረቃል፣ የታመመው ይድናል፣ የወደቀው ይነሳል፣ የተጣላው ይታረቃል፣ ያበላሸው ያስተካክላል፣ ያልታየው ያያል፣ የተደበቀው ይገለጻል፣ የጠፋው ይገኛል፣ ያጣው ያገኛል፣ የተሳሳተው ይመለሳል እና የመሳሰሉትን ቀና አስተሳሰቦች በማሰብና ለተግባራዊነታቸውም ሌት ተቀን መሥራትን ይፈልጋል። ትዕግሥት እንቅስቃሴ አልባ ሳይሆን በይሁንታዊ ቀና አስተሳሰብ እየተመራ ተግባራዊ እንቅስቃሴን ይፈልጋል።   
በቅዱስ መጽሐፍ እንደምናየው ነቢያት ከፍተኛ ችግር የደረሰባቸው ቢሆንም የሚጠብቁትን ነገር ይሆናል ብለው አምነው ይህንኑም በትዕግሥት ጠብቀዋል። ይህንንም ያዕቆብ ሲገልጽ እንዲህ ይላል “ወንድሞች ሆይ፥ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ።” (ያዕቆብ 5:10) በያዕቆብ መልዕክት ምዕራፍ 1:2-4 እንደተጠቀሰው በእምነታችን ላይ ለሚመጣው ፈተና ትዕግሥት ሥራውን እንዲሠራ ሁኔታውም ሲከሰት ደስ ሊለን እንደሚገባ ያስረዳል። ፈተና በቀና ለሚመለከቱትና ለተዘጋጁ ተማሪዎች ከክፍል ወደ ክፍል እንደሚያሳልፍ ሁሉ በሕይዎትም የሚገጥም ችግር ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያሸጋግር እሙን ነው። የፈጠራ ሥራዎች የችግር መፍትሄዎች ናቸው። “ችግር ብልሀትን ይፈጥራል” እንደሚባለው።   
መከራን በመታገስ ዋነኛ ስፍራ ከሚይዙት ውስጥ ኢዮብ አንዱና ታላቁ ነው። ኢዮብም መታገሱን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርም እንደፈጸመለትም መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። “እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።” (ያዕቆብ 5:11) የእግዚአብሔር ለሚታገሡት ምህረቱ እምን ነው።
ብዙ ፈታኝ ነገሮች በሩቅም ተፈጽመው ተመዝግበው ያሉም ሆነ አሁን በቅርብ ዘመን የተከሰቱት ትዕግሥትን የጠየቁ ነገሮች በአብዛኛው ረጂም ጊዜን ወስደዋል። እስራኤላውያን በነቢዩ ሙሴ እየተመሩ ከግብጽ ወጥተው ወደ ቃል ኪዳን መሬት ሲሄዱ ጉዞው እልህ አስጨራሽ ከመሆኑም በላይ ብዙ ዓመታትን (40 ዓመታት) ወስዷል። ብዙዎችም ወገኖቻቸው እንደሚደርሱ ከማመን በስተቀር ባይናቸው ለማየት አልበቁም። ተመሳሳይነት ያላቸው ከዚያ ቀረብ ያሉ ብዙ ክስተቶችንም መጥቀስ ይቻላል። ይህንንም ለአንባቢዎቸ እተወዋለሁ።
በእግዚአብሔር ለሚያምኑና መንፈሳውያን ለሆኑ ሕይዎታቸውን ለጌታ ለእየሱስ ክርስቶስ ለሰጡ የመንፈስን ፍሬዎች ማፍራት እንዳለብን ሐዋርያው ጳውሎስ ሲያስተምረን ፍሬዎች ብሎ ከገለጻቸው ውስጥ “ትዕግሥት” አንዱ ነው።  እግዚአብሔርም ለሰው ልጆች በአካል የተገለጸ ባይሆንም መልካም እንደሚያስብ በነቢዩ ኤርሚያስ “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።” (ኤር 29:11) ሲል ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል። መልካሙንም ነገር ሁሉ በጊዜው ያደርጋል ብሎ በእምነትና በትዕግሥት መጠበቅ መንፈሳዊ ፍሬ የማፍራት ምልክት ነው። 

... በሚቀጥለው ትዕግሥት ለምን ያስፈልጋል? እና የሚፈታተነንን ወይም ጊዜ የሚውስድን  ነገር እንዴት ልንታገእንችላለን? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ያለኝን ሐሳብ አቀርባለሁ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ነጋ ዓለማየሁ

Finding Hope in a Hopless environment

Finding hope in a hopless environment
It is true that in the world of today, it is very easy to lose hope because of the broken things that we see here and there. It seems that no body has control over anything. How can I be certain about my future? How can I fix things aroud me? I see so many things falling apart. “What a curse!” could be the words that one sees in the back of his mind.
This happens when you pass on the remote control to another person. Expecting others to fix the environment around me and make me feel good is like giving them my remote control. They can turn me OFF or ON. That is like I am in their mercy.
I must take responsibility to whatever happens around me. When I am responsible I am able to respond (response-able) to any stimulus. It is my response to whatever happens around me that causes my emotional status. I must make a choice that brings benefit to myself as well as others. I may be in a situation where people regularly argue and fight, I may be in a situation where someone gets mad at me, I may be in a situation where material needs are not fulfilled, etc. Now the question is “How do I respond to such situations?” Definitely, the common thing to do is respond accordingly. If someone screams at you scream back; if members of the family are arguing get involved in the conversation and shout at them. Would this help? No. It is like turning the lights off during night time. 
Whenever there is misunderstanding and problems it is said to be darkness everywhere. It is important that a candle light during night time helps a great deal. I can become the candle light and let those who argue to see each other rather than letting them step on each other’s toe in the darkness. That brings benefit to the self and others. God is the light. Whenever He is invited there won’t be any darkness. Darkness and light can’t live together. That is why we have to keep God in our hearts. You become the little candle that gets its energy from the supreme eternal light, God. Remember you can be a source of inspiration for people around you. People will always see those who are stable emotionally at the time of crisis.
Take a break from the mundane life and reflect on the characters of GOD. Pray and get the energy that you need from time to time. Don’t be in a rush to fix problems that existed for long time. It took the Israelites 40 years to get to the Promised Land even with the direct supervision of the Almighty God. Moses didn’t make it to the Promised Land. Patience in faith is important. That means believing that things around me will change to the better and working towards achieving it. 
... will continue. 


Nega Alemayehu

Wednesday, October 5, 2011

መልካም አስተሳሰብ

ስለቀና አስተሳሰብ ብዙ ተብሏል። ምን እንደሆነ ከማስረዳት ጀምሮ ሊያመጣው የሚችለውን ነገር በመተንተን የሃይማኖት ሰዎችም ሆኑ የስነ  ልቦና  ጠበብቶች ብዙ ይናገራሉ ይጽፋሉ። ጉዳዩን ለማሳወቅም ሆነ  ለማወቅ ጊዜ  የሚጠፋበት ምክንያት ከፍተኛ  ጠቀሜታ ስላለው ነው። ጠቃሚነቱም የሚመነጨው ሀሳብ ጉልበት (Energy) ነው ከሚለው ነው። ጉልበት ነው ስንል በአንድ በኩል አዎንታዊ ጉልበት ሊሆን ሲችል በሌላ  በኩል ደግሞ ኢ_አዎንታዊ (Negative) ሊሆን ይችላል።


ቀና  አስተሳሰቦች አዎንታዊ ጉልበት ያመነጫሉ ኢ_አዎንታዊ አስተሳሰቦች ደገሞ ተቃራኒውን በጎ ያልሆነውን ባለቤቱንና አካባቢውን የሚጎዳውን ጉልበት ያመነጫሉ።  ታዲያ  የዚህን  ምስጢር የተረዱ ምርጫቸው  ቀና  አስተሳሰብ እንዲሆን ይጥራሉ። በአገራችንም "ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ" የሚል አባባል አለ። ቀና አስተሳሰብ በመጀመሪያ የሚጠቅመው ባለቤቱን ነው። ቀና ያልሆነ አስተሳሰብም ደግሞ በመጀመሪያ  የሚጎዳው ሃሳብ አሳቢውን ባለቤቱን ነው። ይህም በኒውተን የድርጊት ሕግ (Newton's Law of Action - for each action there is an equal and opposite reaction) ከሚለው ጋር የሚሄድ ይሆናል። ስለዚህ ቀና  ሃሳብ ያሰበ  የቀናውን ውጤት ያገኛል።  በተቃራኒው ያሰበ  ደግሞ ለአስተሳሰቡ ተገቢ የሆነውን ቀና ያልሆነውን ውጤት ያገኛል። አንድን ነገር ለመሥራት የተነሳሳ ሰው ቀና  ውጤት ለማግኘት አንደሚችል ከወዲሁ ማሰብ ይኖርበታል። ቀና ያልሆነ ነገር እያሰብ የሚሳካለት ሰው ብዙ አይኖርም። 
ስፖርተኞች አሸናፊነታቸውን  ከማረጋገጣቸው በፊት  በአእምሮአቸው አሸንፈው ማየት ይኖርባቸዋል።  ያ  ቀና  አስተሳሰብ ነው ለድል 
የሚያበቃውን  ጉልበት የሚያመነጨው።መውደቁን የሚያስብ ተማሪ ውጤቱ መውደቅ  ይሆናል። ስለዚህ በማንኛውም ጉዳይ ዙሪያ በይሆናል ቀና  አስተሳሰብ መሄድ ለጤናም መልካም ከመሆኑ ባሻገር ለሁኔታው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ማሸነፉን እየተጠራጠረ  ውድድር ውስጥ የሚገባ  ስፖርተኛ  ያሸንፋል ብዬ አላስብም።   አሸናፊ የሚሆኑት ሁሉ በማሸነፋቸው ቆርጠው የገቡ ናቸው።

... ይቀጥላል

Tuesday, October 4, 2011

ፍቅር ምንነቱና አስፈላጊነቱ

ነጋ ዓለማየሁ 
ሲልቨር ስፕሪንግ፣ ሜሪላንድ

1.    ፍቅር
ፍቅር ትልቁና ዋነኛ ነገር እንደሆነ እየሱስ ክርስቶስ እራሱ አስተምሯል። ፍቅር አንድን ሰው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል ነው እግዚአብሔር እንዲሁ አለምን ወዷልና። "በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይዎት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና።" (ዮሐ 3፡16) ስለተደረገልን ነገር ብለን ሳይሆን እንዲሁ ስንወድ ፍቅር ይባላል። ፍቅር ተቀብሎ በመስጠት ሂሳብ የተመሰረት አይደለም። በዚህም ምክንያት ፍቅር ትልቅ ግንኙነትን የማዳን ኃይል አለው። ፍቅር ከጥላቻ የበለጠ አቅም አለው። ማፍቀር በእግዚአብሔር ለሚያምኑ የግድ ነው። ይህንንም አስመልክቶ ቅዱስ መጽሐፍ “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።” (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4:8) ይለናል። ስለዚህ ሰዎች ለእኛ ጥሩ በሚሆኑበት ጊዜ ወይም በተሳካላቸው ጊዜ የምንሰጠው ፍቅር ሳይሆን ከዚህም ውጭ ሲሆኑ የምንሰጣቸው ነገር ነው በፍቅር ስጥ ሊካተት የሚችለው። ፍቅር ሰጪ እጁን እንጂ ተቀባዩን አያሳይም።
ለክርስቲያኖች ይህንን መረዳት ቀላል ሊሆን ይገባል። ክንያቱም እግዚአብሔር አንድ ልጁን ለፍቅር መስዋዕት አቅርቧልና። እየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ያደረገው መልካም ነገር ፍቅር አስይዞት አይደለም ራሱን አሳልፎ የሰጠው እንዲሁ ሰውን በማፍቀሩ እንጂ። እኛም የቤተሰብ አባል የሆኑትንም ሆነ ሌሎችን እንዲሁ እንድንወዳቸው ከዚያም የፍቅርን ምላሽ ልናገኝ እንችላለን። ፍቅር አለን የምንልም ሁሉ ከዚህ አንጻር እራሳችን መጠየቅ አለብን። የምናፈቅራቸው ሰዎች አንድ ወይም ሁለት ነገራቸው ቢለወጥ ምን እንላለን? የምንከባከባቸው ሰዎች ባላሰብነው መንገድ ቢሄዱ ምን ይሰማናል? ያለቅድመ ሁኔታ ማፍቀር የሚለው በትክክል ከተረዳነው እነዚህን ሰዎች ስናፈቅራቸው ተበላሸ የምንለው ነገር እንዲድን እግዚአብሔር ይረዳል።
ለሰው መቸም መልካም የሚያደርግለትን መውደድ ቀላል ነገር ነው። የሚጠላውን መውደድ ግን በጣም ከባድ ነገር ነው። ደንጋይ የሚወረውርብህን ውደድ ማለት ሞኝነት ይመስላል። እንዲያውም ሁለተኛ ደንጋይ እንዳይወረውር ቋጥኝ የሚያክል ደንጋይ አንስቶ መውገር የሚሻል ይመስለናል። እግዚአብሔር ግን ሰውን ወደደ ከመውደዱም የተነሳ አንድ ልጁን ለሰው ልጅ የኃጢአት ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ለመስዋዕት እንዳቀረበ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ስጦታ የሚሰጠው ለሚወዱት ነው። እግዚአብሔር ታዲያ በእውን ወዶናልና ታላቁን ስጦታ ሰጠን። ሆኖም ግን የሰው ተግባር ለስጦታ የሚያበቃ ነበር ወይ? ሰው በኃጢአት ደክሞ ይህ ነው የማይባል ርኩሰትን እየፈጸመ ባለበት ጊዜ እግዚአብሔር ግን ታላቁን ነገር አደረገለት።
እግዚአብሔር የሰውን በደል፣ ደካማነትና የመንፈስ ጉስቁልና ሳይመለከት እንዲሁ ወደደው። "አንተ ጥሩ ነህ መልካም ሥራ ሠርተሀል" ብሎ ሳይሆን "አንተ የእኔ ነህ ምንም አድርግ ምንም የእኔ ነህና አልተውህም" በማለት በፍቅሩ ጎበኘው። ትክክለኛው ፍቅር ምንም ቅድመ ሁኔታ የለውምና። ለፍቅር ቅድመ ሁኔታ ከተበጀለት ፍቅር ሳይሆን የንግድ ሥራ ወይም ተቀብሎ ተመጣጣኝ ዋጋ መክፈል ነው። ቅድመ ሁኔታ አበጅተን የሚወዱንን ወይም መልካም ያደረጉልንን ለመውደድ መለኮታዊ ኃይል ወይም መንፈሳዊነት አያስፈልገንም። መንፈሳዊነት የሚያስፈልገው የሚጠሉንንና የሚረግሙንን ለመውደድ ነው።
የደካሞችን ችግር ማየት እንደለለብንና እንዲያዉም ሸክማቸውን ልንሸከም እንደሚገባ የክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።”(ገላትያ 6፡2) ታዲያ ስህተት ብናይም ስህተቱን ለመጋራት መፈለጋችንና የራሳችን እንደሆነ መገንዘቡ ፍቅራችን ያለቅድመ ሁኔታ እንዲሆን ይረዳናል።

1.1 መግቢያ

ፍቅር ከንፈ ፍሬዎች አንዱ መሆኑን የክርስቶስ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ ወደ ገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ "የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።" (ገላትያ 5፡22) እያለ ያስተምረናል። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሁሉም የምትበልጠዋ ትእዛዝ ፍቅር መሆኗን "ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፥ ባልንጀራህን እንደነፍስህ ውደድ የምትለው ናት" (ማቴ 22፡ 37-39) ብሎ ዘላለማዊ በሆነው ቃሉ ያስተምናል። ፍቅርም ለሚያፈቅሩን ወይም በጎ ላደረጉልን ብቻ ሳይሆን የሚጠሉንም ሆነ የሚረግሙንን እንድንወድ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ያዘናል "እኔ ግን እላችኋለሁ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሟችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።" (ማቴ 5፡ 44-45) በመሆኑም ፍቅር ታላቅና አቢይ ነገር ነው ማለት ነው። ዚህ በፍቅር ዙሪያ እግዚአብሔር እንደፈቀደ የሚከተለውን ትንታኔ አቅርቤአለሁ።

1.2 ፍቅር ምንድን ነው?

ፍቅር ዋናና መለወጫ የሌለው ነገር ለመሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። ስለዚህ ዋናው ነገር የፍቅርን ምንነት መረዳቱና መተግበሩ ነው እንጂ አስፈላጊነቱን ማወቁ አይደለም። ለሰው መቸም መልካም የሚያደርግለትን መውደድ ቀላል ነገር ነው። የሚጠላውን መውደድ ግን በጣም ከባድ ነገር ነው። ደንጋይ የሚወረውርብህን ውደድ ማለት ሞኝነት ይመስላል። እንዲያውም ሁለተኛ ደንጋይ እንዳይወረውር ቋጥኝ የሚያክል ደንጋይ አንስቶ መውገር የሚሻል ይመስለናል። እግዚአብሔር ግን ሰውን ወደደ ከመውደዱም የተነሳ አንድ ልጁን ለሰው ልጅ የኃጢአት ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ለመስዋዕት እንዳቀረበ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። ስጦታ የሚሰጠው ለሚወዱት ነው። እግዚአብሔር ታዲያ በእውን ወዶናልና ታላቁን ስጦታ ሰጠን። ሆኖም ግን የሰው ተግባር ለስጦታ የሚያበቃ ነበር ወይ? ሰው በኃጢአት ደክሞ ይህ ነው የማይባል ርኩሰትን እየፈጸመ ባለበት ጊዜ እግዚአብሔር ግን ታላቁን ነገር አደረገለት።
          እግዚአብሔር የሰውን በደል፣ ደካማነትና የመንፈስ ጉስቁልና ሳይመለከት እንዲሁ ወደደው። "አንተ ጥሩ ነህ መልካም ሥራ ርተሀል" ብሎ ሳይሆን "አንተ የእኔ ነህ ምንም አድርግ ምንም የእኔ ነህና አልተውህም" በማለት በፍቅሩ ጎበኘው። ትክክለኛው ፍቅር ምንም ቅድመ ሁኔታ የለውምና። ለፍቅር ቅድመ ሁኔታ ከተበጀለት ፍቅር ሳይሆን ሌላ ቢባል ይሻላል። ቅድመ ሁኔታ አበጅተን የሚወዱንን ወይም መልካም ያደረን ለመውደድ መለኮታዊ ኃይል ወይም መንፈሳዊነት አያስፈልገንም። መንፈሳዊነት የሚያስፈልገው የሚጠሉንንና የሚረግሙንን ለመውደድ ነው።
የክርስትና ሃይማኖት ዋና ፍሬ ነገር (Essence) ፍቅር ይመስለኛል። የሰው ልጅ በአዳም ምክንያት ከገነት ተባሮ በጢአት ዓለም ይኖር ነበር። ምንም እንኳ አዳም በገዛ ሥራው ከገነየወጣ ቢሆንም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከመውደዱ የተነሳ ሊያድነውና ከመጥፎ ሥራው አውጥቶ ወደ ቀደመ ማዕረጉ እንዲመለስና የዘለዓለም የደስታ ሕይዎት ሊሰጠው ፈለገ። ፍቅር ድክመትን አያይምና እግዚአብር አምላክ የሰውን ልጅ ድካምና ጢአት ሳይመለከት ሊያድነው በመውደዱ አንድ ልጁን ወደዚህ ዓለም ላከ። "በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይዎት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና።" (ማቴ 3፡16)
የእግዚአብሔር አብ የባህሪ እኩያ የሆነው እግዚአብሔር ወልድም የእኛን መከራ ተቀብሎ እናንተ አትችሉም እኔ ዕዳችሁን ልክፈልላችሁ ብሎ በጢአተኞች እጅ ተገርፎና በምስማር ተቸንክሮ የጢአታችን ዕዳ ከፈለ። ይህ ለምን ሆነ ቢባል ለፍቅር የተከፈለ ዋጋ ነው ይባላል። በዓለማችንም የሚዋደዱ ቤተዘመዶች ውስጥ አንዱ የተበደረውን የገንዘብ ዕዳ ሌላኛው እንደሚከፍል ሁሉ ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ከዚያም ቀጥሎ የተቆረሰውን ሥጋዬን ብትበሉ የፈሰሰውን ደሜን ብትጠጡ መለኮት ለዘላለም እንደሚኖር ሁሉ እናንተም የዘላለም ሕይዎት ታገኛላችሁ ብሎ አወጀ። ከፍቅሩ ብዛት ሰውም እንደእሱ ለዘላለም ሕይዎት እንዲኖረው አደረገ።
ይህ እንግዲህ አምላክ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ያመለከተ ታላቁና አቢይ ተግባር ሲሆን የፍቅርን ምንነት የገለጸና ያስተማረ ነው። እግዚአብሔር በኦሪት ለሙሴ የሰጠው ሕግጋትም ቢሆን ዋናው ቁም ነገር ፍቅር ነው። እነርሱም ሰው ለእግዚአብሔር፤ ሰው ለባልንጀራው ሊኖረው ስለሚገባ ፍቅር ተብሎ ሊጠቃለል ይችላል። ለዚህም ነው ክርስቶስ ከለይ እንደተጠቀሰው የፊተኛይቱና ሁለተኛይቱ ብሎ የሚገልጻት። አምላክ የሰውን ልጅ እወድሀለሁ ሲለው "ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ" አለው። ለአንተ ያለኝ ፍቅር የጠና ነውና አንተም እኔን ልትወደኝ ይገባል። በመካከላችን ሌላ ልታስገባ አይገባህም ወይም ደግሞ እኔን ልትተካኝ አትችልም ማለቱ ይመስለኛል።
ከዚያም ሰው ለባልንጀራው ሊኖረው የሚገባውን ፍቅር ሲገልጽለት አትግደል፣ አታመንዝር፤ በሐሰት አትመስክር፤ ንብረቱን አትመኝ እያለ አዘዘው። ሰው የሚወደውን አይገድልምና፣ ከሚወደው ላይ አያመነዝርምና፣ በሚወደው ላይ በሐሰት አይመሰክርምና፣ የሚወደውንም ሰው ንብረት አይመኝምና በአጭሩ አፍቅረው ወይም ውደደው አለው። ሰው እግዚአብርንና ባልንጀራውን ከወደደ ምን ችግር ሊኖርበት ይችላል?
ሰዎች በዘመናችን በትንሹም በትልቁም ጉዳይ ቂም ተያይዘው ይቅር ማለት ይቸግራቸዋል። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት ትክክለኛው ፍቅር ባለመኖሩ ነው። ፍቅር ሁልጊዜ ይቅር ባይ ነው። ለነገሩ ሰው ፍቅር ካለው ቅሬታ የሚባለው ነገር ከመጀመሪያውም አይመጣም። ክርስቶስ ፍቅሩን አይቶ ጢአታችን ሳይመለከት እኛን ለማዳን ከሰማይ እንደወረደ ሁሉ ፍቅር ያለው ሰው የሌላውን ስህተት አያይም። ከዚህ አንጻር ፍቅር እውር ነው ሊባል ይችላል። እውርነቱም ደግ ያልሆነውን ነገር ባማየቱ ነው። በፍቅር የደረጀው ስብዕና ሌላ መጥፎ ነገር ሊያሳየው አይችልም።
በሌላ በኩል ደግሞ ፍቅር አካላዊ ይን ሊያየው የማይችለውን ረቀቅ ያለውን የሰው ልጅ ንጹህ ባህሪ ሊያይ የሚችል አጉሊ መነጽር ነው። በሁለቱ አካላዊ አይኖቻችን ልናየው የማንችለውን ውበትም ሆነ መልካም ባህሪ በፍቅር ግን ልናየው እንችላለን። አባቶቻችን ሲተርቱ "የወለደና የጋገረ ጅል አይልም" ይላሉ። ይህም የሆነበት ምክያት ወላጆች ለልጆቻቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ ነው። ፍቅር ሲኖር ሁሉ ነገር ይኖራል። ፍቅር ትእግሥተኛ፣ ይቅር ባይ፣ ተባባሪ፣ አክባሪ፣ አስተዋይ፣ አዋቂ፣ አንድነት፣ እውነት በመሆኑ ሌላውን በሚገባ ለማየት ያስችላል። ሁሉም ነገር ኑሮት በፍቅር ማጣት የተነሳ እነዚሁ የጎደሉት ሰው አረም የሞላበት ጓሮ እንደማለት ነው። አረም የሞላበት ጓሮ ደስ አይልም። አላፊ ግዳሚውም "ይኸ የሰነፍ ሰው ጓሮ" እያለ ያልፋል። ምንም ንብረት ሳይኖረው ፍቅር ቢኖረው ግን ንጹህ ጓሮ አለውና ያየው ሁሉ ሊከራየው፣ ሊገዛው፣ ጊዜውን ሊያሳልፍበት ይፈልጋል። ከዚያ ጋር ተያይዞም በሚመጣው ሲሳይ ከፍ ያለ ሀብትና ደስታ ያገኛል ማለት ነው።
ስለዚህ በቅርብ የምናውቃቸውንም ሆነ  የእግዚአብሔር ፍጡር የሆነውን ማንኛውንም ሰው   ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ልናፈቅ ይገባል። በኑሮአቸው መልካም ነገር ስለገጠማቸው ወይም ጥሩ ያልሆነ ነገር ስለገጠማቸው የእኛን ፍቅር ሊለውጠው አይገባም። ለምሳሌ ልጀ በትምህርቱ ጥሩ ጤት አላመጣም፤ ባለቤቴ መልካም ነገር አላደረገልኝም/አላደረገችልኝም፤ እከሌ ሰላምታ ከለከለኝ እና የመሳሰሉትን እያልን ፍቅር ከቀነስን ቅድመ ሁኔታ አዘጋጀን ማለት ነው። በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተው ፍቅር ደግሞ ፈተና ይበዛበታል። ከዕለታት አንድ ቀን የተቀመጠው መሥፈርት ቢጓደል ፍቅር ችግር ላይ ይወድቃል። እንደዚሁ ያለውን "ፍቅር" ታዲያ ፍቅር ሳይሆን የህብረት ስምምነት ወይም በውለታ ላይ የተመሠረተ "ፍቅር" ወይም ግኑኝነት ሊባል ይችላል። 

1.3 ፍቅር ለምን ያስፈልጋል?

እግዚአብሔር ሰውን እንዲሁ የበላይነቱን ለማሳየት ሲል ያዘዘው አንዳችም ነገር ያለ አይመስለኝም። ሐኪም አንድ በሽተኛ ከበሽታው እንዲድን መድሐኒት እንደሚያዝለት ሁሉ የሐኪሞች ሐኪም የሆነው ዘመን የማይሽረው እግዚአብሔር አምላክም የሰው ልጅ ጤነኛና ደስተኛ ሆኖ ይኖር ዘንድ ትእዛዛትን ሰጥቶታል። ትእዛዛቶቹም በደስታ፣ በጤንነት፣ በሰላም እንዲኖር የተሰጡት መድሃኒቶች (Prescriptions) ናቸው። አፍቅር የሚለውም ከዚያ የመነጨ ነው።
ሰው በጣም የሚጠላውንና በጣም የሚወደውን ሰው እኩል ነው የሚያስታውሰው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው በሰው ቅር በተሰኘ ጊዜ በጣም በተቀየመ ጊዜ ያንን ያስቀየመውን ሰው አሁንም አሁንም ያስታውሰዋል። ቅር ያሰኘውን ሰው መርሳት ቀላል ነገር አይደለም። እንዲያውም እንደነገሩ አሳሳቢነት ጉዳዩን ያወቁ ቤተሰቦች ወይም ጓደኞች ሁኔታውን ለማረሳሳት ቢሞክሩም በቀላሉ የሚተው አይደለም። በተመሳሳይ ሁኔታም የሚወደውን ሰው አሁንም አሁንም ያስታወሳል። በሁለቱ መካከል በማስታዎስ ረገድ ልዩነት አይኖርም። ሆኖም ግን ሐሳቦቹ ያላቸው ተጽእኖ ልዩነት የሲኦልና የገነት ያህል ነው።
          ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው የጠላውን ሰው ባስታወሰ ጊዜ ተጠይው የተናገረው መጥፎ ቃል ወይም ያደረገው መጥፎ ድርጊት ይታወሰውና እያንዳንዷ ትእይንት ኢአወንታዊ (Negative) ኃይል ሆና ሰውየውን ቀስ በቀስ መንፈሱን ታደክመዋለች፥ የአካሉ ሕዋሳቶችም የሥራቸውን ሂደት ለወጥ ያደርጋሉ። ይኸ ሰው በዚያ ሰዓት ፊቱን በመስታዎት ቢመለከት ጥሩ ያልሆነ ሃሳብ ምን አይነት ተጽእኖ እንዳለው መረዳት ይችላል። ጨጓራውም አሲድ ይረጭና ማቃጠል ይጀምራል። መላው የሰውነት ህዋሳትም በጣም ስሜታዊ (sensitive) በመሆኑ የደም ግፊቱም ይጨምራል። ይህ ከብዙ በጥቂቱ የሚያደርሰው ችግር ነው። የሚገርመው ነገር ተጠይው ሰው ይህን ያህል ጉዳት ማድረሱን አለማወቁ ነው።
          በተቃራኒው ደስ የሚለንን ነገር ወይም የምንወደውን ሰው ባስታወስን ጊዜ የሰውነታችን ህዋሳቶች ሁሉ ይፍታታሉ። ፊታችን ሁሉ በፈገግታ ይሞላል። በዚያ ወቅትም የሙሉ ጤነኛ ስሜት ይሰማናል። እራሳችን በመስታዎት ብናይም በቅሬታ ጊዜ ከምናየው ጋር ያለውን ልዩነት እናያለን። ታዲያ ማን አለ ልጁ በሥጋው እንዲሰቃይ ወይም ችግር እንዲደርስበት የሚፈልግ? ወላጆች ልጆቻቸውን ምንም ወንጀል እንዳይሠሩ ይመክራሉ። ይኸንም የሚያደርጉበት ምክንያት ልጆቹ ወንጀል ከሠሩ የሚደርስባቸውን ቅጣት ስለሚያውቁ ነው። በተመስሳይ ሁኔታ ጊዜ የማይወስነው፤ ያለፈውን፣ የአሁኑን የወድፊቱንም የሚያውቀው እግዚአብሔር አምላካችን አባታችን ለልጆቹ ሰላም ሊሰጣቸው፤ ደስተኛና ጤነኛ ሊያደርጋቸው የሚችለውን ነገር ትእዛዝ ብሎ ሰጥቶናል። ለዚህም ነው 'አፍቅር' ብሎ ያዘዘን።
ሐኪም የታዘዘልህን መድሐኒት ካልወሰድክ በሕይወትህ ላይ ችግር ታመጣለህ እንደሚለው ሁሉ፥ እግዚአብሔርም ካላፈቀርክ በምድርም በሥጋህ ስቃይን ታበዛለህ። በኋላም ለነፍስህ ዘላለማዊ ሕይዎት የሚገጥምህ አሁን የዘራኸው የዘርህ ፍሬ አዝመራ ነውና መልካም ነገር አይገጥምህም። ጎበዝ ገበሬ መልካም አዝመራ ከማዝመሩም በተጨማሪ ከወዲሁ ደስተኛ እንደሚሆን ሁሉ እኛም የፍቅርን ህግ ካከበርን በምድርም ደስተኞች እንሆናለን።

1.4 የሚጠሉንን እንዴት ልንወድ እንችላለን?
"መቀየሜን ትቸ ማፍቀር እንዳለብኝ እኮ ይገባኛል። ኖም ግን እንዴት ይቻላል? ይህ የሚጠሉንን ማፍቀር የሚባለው ነገር ለማለት ካልሆነ በስተቀር ለመፈጸም ከባድ ነው።" እነዚህና የመሳሰሉ አባባሎች የተለመዱ ናቸው። አንዳንድ መምህራን ሳይቀሩ "በእሱ ቸርነት እንጂ በሥራችን አንድንም" ው ይደመድማሉ። ይኸ አባባል እውነታነት አለው። የሚጠሉንን ማፍቀር ቀላል ነገር አይደለም። ለዘመናት አብሮ የቆየን ነገር ማስወገድ ከባድ ነገር ነው። አንድ ባልሆነ ሱስ የተለከፈ ሰው እንኳ ያንን ሱሱን ለመተው በጣም ይቸገራል። ሆኖም ግን ለመተው የቆረጠ እንደሆነ የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅሞ ሊያቆም ይችላል። ይህም ሰው መረዳት ያለበት ነገር በአንድ ሌሊት የሚሆን ነገር አለመኖሩን ነው። ክርስቶስ የሚጠሉንን እንድንወድ እንዲህ ሲል ያስተምረናል "ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፥ የሚረግሟችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድልዋችሁም ጸልዩ" (ሉቃስ 6፡27-28) እግዚአብሔር የማይሆንን ነገር አይናገርም አያዝምና ይህ ቃል ትክክል ነው ማለት ነው። ይ ከሆነ "አይቻልም" የሚለውን የራስን ራዕይና ይኸንኑም የማሳካት ተግባር (Self fulfilling prophecy) ትተን በ"ይቻላል" መቀየር አለብን። ክርስቶስም ተዋደዱ ብሎ ሲያዘን በእሱ ማድረግ የማንችለው ነገር እንደለለ ያበስርልናል።
          ጥላቻን ለማስቀረት ከሚጠቅመው ነገር ዋነኛው ነገር እራስን ማወቅ ነው። የእራስን አካላዊ ወይም ሥጋዊ ማንነት ሳይሆን መንፈሳዊ ማንነትን መረዳት አስፈላጊ ነው። እራስን በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በእድሜ፣ በትምህርት ደረጃ፣ በሙያና በመሳሰሉት ለይቶ ማወቅ ከሥጋ ጋር የተያያዘ እውቅና ነው። ይህ እውቅና ሥጋ ውስን እንደሆነ ሁሉ ውስን ነው። ሥጋና ነፍስም ኮንትራታቸውን ሲጨርሱ የሚቀር ነው። ዋናውና ነጻ የሚያወጣው እውቀት ወይም እውቅና ከእግዚአብሔር የሚገኘው የመንፈስ ወይም የነፍስ እውቅና ነው። ማነታችን በሚገባ ስንረዳ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዮስ ሰዎች በላከው ደብዳቤ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊል 4:13) የሚለው እውን ይሆናል። መንፈሳዊ ማንነትን ሳይረዱ የመንፈስን ባህሪዎች መላበስ አስቸጋሪ ነው።
          ይህንን ጽንሰ ሐሳብ በሚከተለው ምሳሌ መግለጽ እፈልጋለሁ። ወደ አገረ አሜሪካ መግባት የፈለገ ሰው የአሜሪካን ፓስፖርት ወይም የአሜሪካ ቪዛ ያስፈልገዋል። ከእነዚህ አንዱን ካልያዘ የመግቢያ ፈቃድ አይሰጠውም። በተመሳሳይ ሁኔታም ፍቅር የመንፈስ ፍሬ ነውና በሥጋ ባህሪ ልንረዳው ወይም ልንፈጽመው አንችልም። በሥጋ እውቀት የመንፈስን ባህሪ ለመተግበር መሞከር ማለት ወደ አሜሪካ ለመግባት ቪዛ የሌለው የኢትዮጵያን ፓስፖርት እንደማሳየት ማለት ነው። ማንነታችን ስንረዳ ከየትኛው ወገን እንደሆንን ማወቅ ያስችለናል። "እኔ ከማን/የማን ነኝ?" ብሎ ራስን መጠየቅ አስፈላጊ ነው። የእግዚአብሔር መሆናችንን ስንረዳና በእውነት እግዚአብሔር የሚፈቅደውን ስናደርግ የእርሱን ኃይል መጠቀም እንችላለን ለዚህም በመጀመሪያ ጽድቁን እንድንሻ "ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።" (ማቴ 6፡33) እያለ ክርስቶስ በሕያው ቃሉ የሚያስተምረን።