ኃላፊነት
የሰው ልጅ ማንም ከማንም ሳይበልጥ እና ሳያንስ እኩል ስጦታ ይሰጠዋል። ስጦታውም የጊዜ ስጦታ ነው። ለምሳሌ ያህል ሁሉም ጧት ሲነሳ እኩል 24 ሰዓታት ይሰጠዋል። አንዱ ብዙ ሥራ አለበትና ብዙ ሰዓታት ያስፈልገዋል አይባልም። በሌላ በኩልም እከሌ ብዙ ሥራ ስለሌለው ሰዓት የቀነስበት አይባልም። ሁላችንም እኩል 24 ሰዓታት ይሰጠናል። የተሰጠነን 24 ሰዓታት አጠቃቀማችን ልዩነትን ይፈጥራል። አንዳንዱ በኃላፊነት ስሜት እያንዳንዷን ደቂቃ ይጠቀምባታል፣ በተገቢ ሁኔታም ያሳልፋታል። አንዳንዱ ደግሞ ደቂቃዎች አይደሉም ሰዓታት እንደ አልባሌ ይባክናሉ። ለእራስ ከመባከናቸውም ባሻገር ለሌሎችም መልካም ያልሆነ ግብአት የሚሆን ነገር ሊተገብሩ ይችላሉ።
ማንኛውም ክንዋኔ መሠረቱ ወይም ዘሩ ሐሳብ ነው። ከ24 ሰዓታት ውስጥ ለማሰብ የሚዉሉ አሉ ፣ ለመናገር ወይም ለመጻፍ የሚዉሉ አሉ፣ ለተግባራዊ ክንዋኔም የሚዉሉ አሉ። ከሐሳብ ጀምሮ ያለው ነገር ጉልበት ነውና በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባል። ሐሳብ ጉልበት (Energy) ነው። ሐሳብ በምናስብበት ጊዜ ጉልበት እየላክን ነው። የጉልበቱ መጠን የሚለካው በሐሳቡ ጥንካሪ ነው። ጠንካራ ፍላጎት ባለው ሰው የታሰበ ሐሳብ ከፍተኛ ጉልበት አለውና በቀላሉ ወደተግባር የተረጎማል። ታዲያ ይህን የተገነዘቡ ሰዎች ስለሚያስቡት ነገር ይጠነቀቃሉ። ለምን ቢባል ተግባራዊ ይሆናልና። ስለዚህ ሰዎች በአካል ስለሚያከናውኑት ተግባር ብቻ ሳይሆን በአእምሯቸው ስለሚያስቡት ሐሳብም ጥንቃቄና ኃላፊነት ይወስዳሉ። ለምን ቢባል ማን እንደሚቀበለውና ተግባራዊ እንደሚያደርገው አይታወቅም። ስለሆነም ሰለእራሳችንም ሆነ ስለቤተሰብ ከዚያም ከፍ ብ ሎ ስለማህበረሰብና አገር የምናስበውን ነገር ጥ ንቃቄ ልናደርግበት ይገባል። መልካም ያልሆነን ሐሳብ መተው እንጂ መያዝ አያስፈልግም። ጉልበት ነውና አንዱ ሊጠቀምበት ይችላል። ስለዚህ ይህን ተገንዝበን ኃላፊነት እንውሰድ። መልካም መልካሙን እንስብ፣ መልካሙን እንናገር፣ መልካሙን እንተግብር። የሐሳብም፣ የቃላትም ሆነ ሆነ የተግባር ተመጣጣኝ ምላሽ ወደ ባለቤቱ ይመለሳልና መልካሙን በጥንቃቄ እንምረጥ።ነጋ ዓለማየሁ
3/20/2019
No comments:
Post a Comment